መጋቢት 15/2013 (ዋልታ) – በዘንድሮ አጠቃላይ ምርጫ የመራጭ ትምህርት ለመስጠት ከ155 በላይ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የተመዘገቡ ሲሆን፣ ምርጫውን ለመታዘብ ከ36 ድርጅቶች በላይ በመጀመሪያ ዙር መመዝገባቸው ተገለጸ።
ምርጫ የዴሞክራሲያዊ ስርአት አንዱ መገለጫ በመሆኑ ሁሉን አቀፍ፣ ነፃ እና ገለልተኛ እንዲሆን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሚና ከፍ ያለ መሆኑን በኢትዮጵያ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ ተናግረዋል፡፡
ሰብአዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ ህዝቡን በማንቃት ብሎም ድርጅቶች በተገቢው መንገድ መሳተፋቸውን በመቆጣጠር በቀጣዩ ምርጫ ላይ ተሳታፊ ለማድረግ እየሰሩ መሆናቸውንም አብራርተዋል።
ቀጣዩን ሀገራዊ ምርጫ በተመለከተ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ልዩ እቅድ አውጥቶ በመስራት ላይ ይገኛል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ በዚህም የመራጭ ትምህርት ለመስጠት ከ155 በላይ ድርጅቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።
በአገሪቱ ያሉ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በተመለከተ ተቋሙ ባወጣው የምዝገባ ሂደት ከ1ሺህ 300 በላይ አዲስ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች መመዝገባቸው የተነገረ ሲሆን፣ 1 ሺህ 805 ድርጅቶች በድጋሚ የምዝገባ ሂደት ተሳታፊ ለመሆን ችለዋል ተብሏል።
በየአመቱ የሚከበረውን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ቀን በተመለከተ ”የመንግስት የሲቪል ማህበራት እና የግል ድርጅቶች ትብብር ለጋራ ልማታችን” በሚል መርህ ከመጋቢት 28 እስከ ሚያዚያ 1 እንደሚከበርም አቶ ጂማ ዲልቦ ገልጸዋል።
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን ጉዞ የሚያስዳስስ ኤግዚብሽን፣ ባዛር፣ ሲምፖዚየም እና በዶክመንተሪ ፊልሞች የታገዘ ዝግጅቶች የበአሉ አከባበር ሂደቶች መሆናቸውን ተናግረዋል።
(በቁምነገር አህመድ)
(በቁምነገር አህመድ)