ሚያዚያ 18/2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) ጠቅላላ ጉባኤውን በ2ወራት ጊዜ ውስጥ ማለትም እስከ ሰኔ 18 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ በድጋሚ እንዲያካሂድ ውሳኔ አስተላለፈ።
ቦርዱ ውሳኔውን ያሳለፈው አብን መጋቢት 23 ቀን 2014 ዓ.ም ያደረገውን ጠቅላላ ጉባኤ አስመልክቶ የቀረበለትን ሪፖርት ከመረመረ በኋላ ነው።
በዚሁ መሠረት፥
1ኛ. ፓርቲው ይህ ውሳኔ ከተገለጸበት ከሚያዝያ 18 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ በ 2ወራት ጊዜ ውስጥ ማለትም እስከ ሰኔ 18 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ ጠቅላላ ጉባኤ እንዲያካሂድ፣
2ኛ. ፓርቲው በደንቡ መሰረት የሚቀርጻቸውን ሌሎች አጀንዳዎችን ጨምሮ በጉባኤው የመነጋገር መብቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ከዚህ ቀደም እልባት ያላገኘው አጀንዳ ማለትም “የአመራር ሪፎርም ወይም ለውጥ ማድረግ” የሚለው ለጉባኤው በአጀንዳነት ቀርቦ ተገቢው ውሳኔ እንዲሠጥበት እና አግባብነት ያለው ምርጫ እንዲደረግ፣
3ኛ. ፓርቲው የመተዳደሪያ ደንቡ አንቀፆች ላይ ማሻሻያ በማድረግ ማሻሻያ የተደረገባቸው የመተዳደሪያ ደንቡ አንቀፆች የተካተቱበትን ረቂቅ መተዳደሪያ ደንብ ጉባኤው ከሚካሄድበት 5 የስራ ቀናት አስቀድሞ ለቦርዱ እንዲያቀርብ፣
4ኛ. ከላይ የተገለፁት ማስተካከያዎች የተደረገበት እና በቦርዱ በቅድሚያ የታየ የተሻሻለ የመተዳደሪያ ደንብ ለጠቅላላ ጉባኤው አቅርቦ በማጸደቅ እንዲያቀርብ፣
5ኛ. ጉባኤው በተጠናቀቀ በ5 ቀናት ውስጥ የጉባኤውን ዝርዝር ሂደት እና ውሳኔ የሚገልጽ ቃለ ጉባኤ፣ በጉባኤው የፀደቀውን መተዳደሪያ ደንብ እና የጠቅላላ ጉባኤውን ሪፖርት እንዲያቀርብ የወሰነ መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል፡፡
ቀደም ሲል በተደረገው የፓርቲው ጉባኤ ቦርዱ ሂደቱን በተሟላ ሁኔታ ለመታዘብ ይችል ዘንድ በቦርዱ የተመደቡት ባለሙያዎች ሂደቱን ለመቅረጽ ሲጀምሩ በፓርቲው አመራር የተከለከሉበት ሁኔታ ፓርቲው ሊያከብረው ከሚገባው፣ በአዋጅ 162 አንቀጽ 16 መሰረት ቦርዱ አዋጁን ለማስፈጸም በሚሰራቸው ተግባራት ከቦርዱ ጋር የመተባበር ግዴታ ተጻራሪ መሆኑ ታውቆ የቦርዱ ባለሙያዎች በቀጣይ ጉባኤ የሚያደርጉትን የሙያ ትዝብት ስራ፣ አስፈላጊ በሆነ መንገድ ሁሉ (ቀረጻን ጨምሮ) ያለምንም ተጽእኖ መከወን እንዲችሉ ፓርቲው ተገቢውን እንዲፈጽም ቦርዱ አሳስቧል።