ምንጩ ያልታወቀ ንብረት አካብቶ በተገኘው የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል መርማሪ በነበረ ግለሰብ ላይ ክስ ተመሰረተ

ግንቦት 12/014 (ዋልታ) ከህጋዊ የወር ገቢው ጋር የማይመጣጠንና ምንጩ ያልታወቀ 9 ሚሊየን ብር የሚጠጋ ንብረትና ገንዘብ አካብቶ በተገኘው የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል መርማሪ በነበረ ግለሰብ ላይ ክስ ተመሰረተ፡፡
በፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ መርማሪ ሆኖ ሲሰራ የነበረው በላይነህ ዳጌቦ ወይም በሀሰተኛ መታወቂያ ስሙ ተመስገን ማርቆስ እየተባለ የሚጠራው ተከሳሽ ከሚያዝያ 01 ቀን 2001 ዓ.ም እስከ ሐምሌ 01 ቀን 2013 ዓ.ም ባሉት ጊዜያት የወንጀል መከላከልና መርማሪ ሆኖ ተቀጥሮ ሲሰራ መቆየቱ ተመላክቷል፡፡
በዚህ ወቅትም በአጠቃላይ ያገኝ የነበረው 453 ሺሕ 838 ብር ሆኖ እያለ ተከሳሹ ግን በመንግሥት ሥራ ተቀጥሮ ያገኝ ከነበረው ህጋዊ ገቢ ጋር በፍፁም የማይመጣጠን 8 ሚሊየን 995 ሺሕ 749 ብር በሀሰተኛ መታወቂያና ማንነት በተከፈቱ የባንክ ሂሳቦች የተለያየ መጠን ያላቸውን ገንዘቦች ያንቀሳቀሰ እና ሁለት የመኖሪያ ቤት አፍርቶና አካብቶ መገኘቱ በማስረጃ መረጋገጡ ተገልጿል፡፡
በዚህ መሰረትም ተከሳሽ በፈፀማቸው ሀሰተኛ የሕዝባዊ ድርጅት ሰነዶች መገልገል፣ በወንጀል ድርጊት የተገኘን ንብረት ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብና ምንጩ ያልታወቀ ንብረትና ገንዘብ በማፍራት የሙስና ወንጀሎች ክስ ተመስርቶበታል፡፡
ክሱን የተመለከተው የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ፀረ ሙስና ወንጀል ችሎት የተከሳሽን የመጀመሪያ የክስ መቃወሚያ ለመጠባበቅ ለግንቦት 22 ቀን 2014 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ መሰጠቱን የፍትህ ሚኒስቴር በማኅበራዊ ትስስር ገጹ አስታውቋል፡፡