ምክር ቤቱ በኢትዮጵያና ቱርክ መካከል የተደረጉ ወታደራዊ ስምምነቶችን አጸደቀ

ግንቦት 9/2014 (ዋልታ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 7ኛ መደበኛ ስብሰባው በኢትዮጵያና ቱርክ መንግስታት መካከል የተደረገውን የወታደራዊ ማዕቀፍ ስምምነት፣ የወታደራዊ ፋይናንስ ትብብር ስምምነትና የፋይናንስ ድጋፍ ማስፈጸሚያ ፕሮቶኮልን መርምሮ አጸደቀ።

ኢትዮጵያና ቱርክ የወታደራዊ ትብብር ለማድረግ የሚያስችላቸውን የወታደራዊ ማዕቀፍ ስምምነት ነሐሴ 12 ቀን 2013 ዓ.ም በቱርክ አንካራ ከተማ መፈራረማቸው ይታወሳል፡፡

ስምምነቱ በሁለቱ ሀገራት መካከል በመከላከያ ዘርፍ የሚደረገው ግንኙነት የሚመራበትን ግልጽ ማዕቀፍ ለመፍጠር ያለመ ነው።

አዋጁ በመከላከያ ኢንዱስትሪ፣ መረጃ ልውውጥ፣ ሎጅስቲክ፣ ጤና አገልግሎት፣ የመረጃ ስርአትና ሳይበር ጥቃትን መከላከልና በሌሎች ተያያዥ መስኮች ላይ በትብብር ለመስራት የሚያስችሉ ድንጋጌዎችን ያካተተ ነው።

በዚህም የባለሙያዎች፣ የቁሳቁስ፣ የመረጃና የልምድ ልውውጥን በስምምነቱ መሰረት ተግባራዊ ማድረግ ያስችላል።

በተጨማሪ የመከላከያ ትብብር መስኮችን በተመለከተ በሁለቱ ሀገራት በትምህርትና ስልጠና በተናጠል ወይንም በጋራ በሚዘጋጁ ወታደራዊ ልምምዶች መካፈልን ያስችላል።

ስምምነቱ ኢትዮጵያ የመከላከያ ኢንዱስትሪ ግብዓቶችን፣ የሎጅስቲክ አቅርቦትንና ድጋፎችን እንድታገኝ እንዲሁም በሰው ኃይልና አስተዳደር ዙሪያ ልምድ እንድትቀስም እንደሚያግዝም እንዲሁ፡፡

በተመሳሳይ በኢትዮጵያና ቱርክ መካከል የተደረገው የወታደራዊ ፋይናንስ ትብብር ስምምነት ሁለቱ አገሮች በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸው መሆኑ ተገልጿል።

ምክር ቤቱ የፋይናንስ ድጋፍ ማስፈጸሚያ ፕሮቶኮል አዋጆችን ጨምሮ ስምምነቶቹ ለኢትዮጵያ የሚያስገኙትን ጥቅም ላይ በመወያየት በሙሉ ድምጽ አጽድቋቸዋል።

በሌላ በኩል ምክር ቤቱ በኢትዮጵያና በዓለም አቀፍ የግብርና ልማት ፈንድ መካከል ለገጠር ፋይናንስ ስርዓት ማሻሻያ መርሃ ግብር ለማስፈጸም የተደረገውን የብድር ስምምነት በ3 ተቃውሞ በ8 ድምጸ ታቅቦ በአብላጫ ድምጽ ማጽደቁን ኢዜአ ዘግቧል።