ጥቅምት 24/2014 (ዋልታ) የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚያደርገውን ክትትልና ቁጥጥር ማጠናከር እንዳለበት በአፍሪካ የአመራር ልህቀት አካዳሚ በስልጠና ላይ የሚገኙ የምክር ቤት አባላት አሳሰቡ፡፡
ለአዲስ የምክር ቤት አባላት እየተሰጠ ያለው ስልጠና ዛሬም የቀጠለ ሲሆን በህግ አወጣጥ፣ በክትትልና ቁጥጥር ዙሪያ በተሰጠው ስልጠና ከምክር ቤት አባላት በርካታ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ቀርበው ሰፊ ውይይትና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
ቀደም ባለው ምክር ቤት ሊያሰሩ የሚችሉ ህጎች ቢወጡም ህዝብን ያላሳተፉና ጥራት የጎደላቸው እንዲሁም ግለሰቦችን ብቻ መሰረት ያደረጉ ህጎች ይወጡ እንደነበሩ በአስተያየታቸው አንስተዋል፡፡
ክትትልና ቁጥጥርን በተመለከተም በርካታ ክፍተቶች እንደነበሩ ጠቁመው በተለይ በፕሮጀክቶች አፈጻፀም ላይ ምክር ቤቱ በሚያደርገው ምልከታ ላይ ውጤታማ ስራ አለመሰራቱንም በክፍተት አስቀምጠዋል፡፡
በቀጠይም የምክር ቤቱን አሰራር በአይሲቲ ለማዘመን፣ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ህጎች እና የማህበረሰቡን ችግር የሚፈታ ጠንካራ የክትትልና የቁጥጥር ስርዓት ለመዘርጋት ምን ታስቧል? የሚሉ ጥያቄዎች በዋናነት ተነስተዋል፡፡
ለቀረቡት ጥያቄዎች ስልጠናውን በሰጡት አቶ ዘካሪያስ ኤርኮላ፣ በኤሊያስ ኑር (ዶ/ር)፣ በአቶ አደባባይ አባይ እንዲሁም በክቡር አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
የምክር ቤቱ ዋና አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ክትትልና ቁጥጥርን በተመለከተ ምክር ቤቱ በርካታ ጠንካራ ስራዎች የመስራቱን ያህል የታዩ ክፍተቶች እንደነበሩ ጠቁመዋል፡፡
የነበሩ ክፍተቶችን ለመቅረፍና በቀጣይ ጠንካራ ተግባራትን ለማከናወን ምክር ቤቱ ጨምሮ ከከፍተኛ ተቋማት እና ከባለድርሻ አካላት በተውጣጡ ባለሙያዎች ከዚህ ቀደም ክትትልና ቁጥጥር ይደረግበት የነበረውን ቼክ ሊስት መመርመሩን ገልጸዋል፡፡
በምርመራውም የክትትልና ቁጥጥር ተግባራቱ ዝርዝር ጉዳይ ላይ ያተኮሩና የተበታተኑ ሆነው መገኘታቸውን አመልክተዋል፡፡
በቀጣይ የክትትልና ቁጥጥር ስራው በዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ብቻ ያተኮረና ውጤታማ የሚያደርግ እንዲሁም የሌሎች ሀገራትን ተሞክሮ ያካተተ የክትትልና ቁጥጥር ሰነድ መዘጋጀቱንም ነው በምላሻቸው ያብራሩት፡፡
አክለውም የምክር ቤቱን ስራ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የማዘመን ስራ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው እስካሁንም ምክርቤቱ የሚሰራባቸው የተለያዩ ሶፍት ዌሮችን በማበልጸግ ወደ ስራ የማስገባት፡ የተለያዩ ሰነዶች ወደ ዲጂታል የመቀየር ስራዎች መከወናቸውን አስረድተዋል፡፡
በቀጣይም በምስልና በድምፅ ተቀርፀው የተቀመጡ ሰነዶችን ወደ ዲጂታል የመቀየርና ፈጣንና ዘመናዊ የመረጃ ልውውጦችን የሚያሳልጡ አሰራሮች ተግባራዊ እንደሚሆኑ መናገራቸውን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡