ምክር ቤቱ የጎፋ ዞን ከአጎራባች ሕዝቦች ጋር በክልል እንዲደራጅ ወሰነ

ሐምሌ 24/2014 (ዋልታ) የጎፋ ዞን ሕዝብ ምክር ቤት የጎፋ ሕዝብ ከሌሎች አጎራባች ሕዝቦች ጋር በክልል እንዲደራጅ ወሰነ፡፡

የጎፋ ዞን ሕዝብ ምክር ቤት በ4ኛ ዙር 9ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 5ኛ መደበኛ ጉባኤው አዲሱ የክልል መዋቅር ተግባራዊ እንዲሆን ወስኗል።

የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ጌትነት በጋሻው (ፒኤችዲ) የጎፋ ሕዝብ የክልል ጥያቄ አደረጃጀትን በተመለከተ ለምክር ቤቱ አባላት ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ባለፉት ሦስት ዓመታት የጎፋ ሕዝብ በክልል የመደራጀት ጥያቄውን በየደረጃው ባሉ ምክር ቤቶች በማስፀደቅ ለሚመለከተው አካል ሲያቀርብ መቆየቱን ዋና አስተዳዳሪው ገልጸዋል።

በአዲሱ የክልል አደረጃጀት በጋራ የሚደራጁ 11 መዋቅሮች ወላይታ፣ ጋሞ፣ ጎፋ፣ ጌዴኦ፣ ኮንሶ፣ አማሮ፣ ደቡብ ኦሞ፣ አሌ፣ ባስኬቶ፣ ቡርጂ እና ደራሼ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ምክር ቤቱ በክልል አደረጃጀት ዙሪያ ተወያይቶ የጎፋ ሕዝብ ከሌሎቹ 10 መዋቅሮች ጋር በጋራ በአንድ ክልል እንዲደራጅ በሙሉ ድምጽ መወሰኑን የደቡብ ክልል መንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ መረጃ አመላክቷል።