መጋቢት 26/2015 (ዋልታ) የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 13ኛው መደበኛ ስብሰባ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት እና ምክትል ፕሬዝዳንት ሹመትን መርምሮ አፀደቀ።
የውሳኔ ሀሳቡን ያቀረቡት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጂጌ ሲሆኑ ሹመቱ በህገመንግስቱ አንቀጽ 81 (2) መሰረት መቅረቡን አብራርተዋል።
በዚህም መሰረት የተሿሚዎቹ የትምህርት እና የስራ ልምድ መረጃቸው የቀረበ ሲሆን የምክር ቤት አባላትም ያላቸው የትምህርትና የስራ ልምድ ለቦታው ብቁ ናቸው ሲሉ ድጋፋቸውን ገልጸዋል።
በመሆኑም በውሳኔ ቁጥር 14 እና 15/2015 ዓ.ም. በሁለት ድምጸ-ተአቅቦ በአብላጫ ድምጽ ሌሊሴ ደሳለኝ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት እና ዛህራ ኡመር አሊ ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው ተሹመዋል፡፡
ይህን ተከትሎም በምክር ቤቱ ፊት ቀርበው ቃለመሀላ መፈፀማቸውን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡