ምክር ቤቱ ጉባኤ ከ253 ሚሊዮን ብር በላይ ተጨማሪ በጀትና ሹመት አፀደቀ

መጋቢት 14/2014 (ዋልታ) የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ምክር ቤት 6ኛ የሥራ ዘመን አንደኛ ዓመት አንደኛ መደበኛ ጉባኤ ከ253 ሚሊዮን ብር በላይ ተጨማሪ በጀትና የቋሚ ኮሚቴ አባላትን ሹመት በማፅደቅ ተጠናቀቀ።
የምክር ቤቱ ጉባኤ የክልሉ ፋይናንስና የምጣኔ ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አሕመድ መሐመድ ባቀረቡት ተጨማሪ በጀቱ ላይ መክሯል።
ተጨማሪ በጀቱ ከክልሉ የውስጥ ገቢ አርዕስቶች እንደሚሸፈን ያመለከቱት ኃላፊው ለተለያዩ የመንግሥት ተቋማት የልማትና መልካም አስተዳደር እንዲሁም የሰላም እሴት ግንባታ ሥራዎች እንደሚውል አብራርተዋል።
በዚህም የቀረበው ከ253 ሚሊዮን ብር በላይ ተጨማሪ በጀት ለተለያዩ የልማት ሥራዎች እንዲውል ምክር ቤቱ መርምሮ በሙሉ ድምጽ ማጽደቁን ከክልሉ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት የተገኘው መረጃ አመላክቷል፡፡
በሌላ በኩል ፍጡማ አደም የህግ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴና ጀሚላ ቡርኡሌ ደግሞ የምጣኔ ሀብት ጉዳይ ቋሚ ኮሜቴ አባል ሆነው እንዲሰሩ በምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ አስያ ከማል አቅራቢነት ምክር ቤቱ በሙሉ ድምፅ በማፅደቅ በሠመራ ከተማ ለሁለት ቀናት ሲያካሄድ የቆየውን ጉባኤ ትናንት ማምሻውን አጠናቋል።