ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር ጋር ተወያዩ

የካቲት 09/2013 (ዋልታ) – የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር ራፋኤል ሞሮቭ ጋር ተወያዩ።

በውይይታቸውም በትምህርት፣ ዲፕሎማሲ፣ ኢንቨስትመንት፣ በባህልና ቱሪዝም ዘርፍ እንዲሁም ከእስራኤል ከተሞች ጋር እህትማማችነት መፍጠርን ጨምሮ ተባብረው ለመስራት በሚያስችላቸው ሁኔታዎች ላይ ተነጋግረዋል።

ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ በሀገራችን ብሎም በከተማችን የሚገኙ ቤተ እስራኤላውያን ያላቸውን አክብሮት ገልፀው፣ በቀጣይም በእስራኤል መንግስትና ህዝብ መካከል ያለውን ጠንካራ ግንኙነት እና ትብብር በይበልጥ ስለማጠናከር ተቀራርበው ለመስራት ዝግጁ ነን ብለዋል።

አምባሳደር ሞሮቭ በበኩላቸው፣ የኢትዮጵያንና እስራኤልን ለዘመናት የቆየ ግንኙነት እና ትብብር አድንቀው፣ በቀጣይም በተጠቀሱት ዘርፎች በጋራ ለመስራት ያላቸውን ፅኑ ፍላጎት መግለፃቸውን ከከተማ አስተዳደሩ ፕሬስ ሴክሬተሪያት ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡