ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር አባይ ከተለያዩ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች ጋር የስምምነት ሰነድ ተፈራረሙ

ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር አባይ

ጥር 16/2014 (ዋልታ) የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባና የስራ፣ ኢንተርፕራይዝ እና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ጃንጥራር አባይ ከ9 የሰራተኛ ፌደሬሽን፣ ከ10 የአሰሪ አደረጃጀቶች እና 3 አስፈጻሚ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች ጋር የስምምነት ሰነድ ተፈራርመዋል፡፡

ኃላፊው ኢንዱስትሪዎች የአገሪቱ ሀብት መሆናቸውን አምነን ያሉ ችግሮችን በጋራ እየፈታን ያደገና የበለፀገን ኢንዱስትሪ እንገነባለን ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ኢንዱስትሪዎች ሰላም እንዲሆኑ የአሰሪና ሰራተኞች አደረጃጀት ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ለተፈጻሚነቱ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ አሳስበዋል፡፡

በቢሮው ኃላፊ ደረጃ የአሰሪና ሰራተኛ ዘርፍ ኃላፊ ዮሐንስ ምትኩ ቢሮው በሁሉም ቦታ በኢንዱስትሪዎች ምቹ የሥራ ሁኔታ እንዲረጋገጥ ከባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ ይሰራል ብለዋል፡፡

ምቹ የሥራ ሁኔታ የሚረጋገጠው ባለድርሻ አካላት በጋራ መስራት በመሆኑ ለተፈጻሚነቱ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ጠቁመዋል፡፡

በዘርፉ የሚከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት፣ ዓላማ፣ የባለድርሻ አካላት ዝርዝርና የሥራ ሁኔታ በቢሮው የኢንዱስትሪ ሰላም የሙያ ደኅንነት ጤንነት ዳይሬክተር ካሳ ስዩም ባቀረቡት መነሻ ሰነድ ላይ አብራተዋል፡፡

የጋራ ስምምነቱ ዓላማ ምቹ የሥራ አካባቢና የሥራ ሁኔታ በመፍጠር የኢንዱስትሪ ሰላምን ማረጋገጥና ምርታማነትን ማሳደግ መሆኑን መናገራቸውንም ከከንቲባ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡