ምዕራባውያን በኢትዮጵያ ታዛዥ መንግሥት እንዲኖር ስለሚፈልጉ የንፁሃንን ጥቃት እንዳላዩ ማለፍ መርጠዋል – አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር)

ዶ/ር አረጋዊ በርሄ

ጥቅምት 11/2014 (ዋልታ) ምዕራባውያንና መገናኛ ብዙሃናቸው በኢትዮጵያ ታዛዥ የሆነ መንግሥት የመመሥረት ፍላጎት ስላላቸው አሸባሪው ሕወሓት በንፁሃን ላይ እያደረሰ ያለውን ጥቃት እንዳላዩ ማለፍ መምረጣቸውን አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) ገለጹ።

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር እና የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሕዝባዊ አስተባባሪ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) እንደገለጹት አሸባሪው የሕወሓት ቡድን የሽብር ተግባሩን በመቀጠል ከሰሞኑ በአማራ ክልል ውጫሌ እና በአፋር ክልል ጭፍራ ላይ በርካታ ንጹሃንን ጨፍጭፏል።

ተላላኪ መንግሥት የመመስረት ዓላማ ያላቸው ምዕራባውያንና መገናኛ ብዙሃናቸው ይህንን የንጹሃን ጥቃት እንዳላየ ማለፍ መምረጣቸውን ጠቁመው፣ መከላከያ ሰራዊት ቡድኑ ለጥፋት የሚጠቀምበትን የግንኙነት ጣቢያ ላይ እርምጃ ሲወስድ በንጹሃን ላይ ጥቃት ያደረሰ በማስመሰል ማራገብን መርጠዋል ብለዋል።

ምዕራባውያን በአንድ ወገን ሽብርተኝነትን እንዋጋለን ይላሉ በተግባር ደግሞ ሽብርተኝነትን እየደገፉ ኢትዮጵያ ነጻና ሉዓላዊት ሀገር ሆና ለመቀጠል ያላትን ቁርጠኝነት በማጨናገፍ ለእነሱ አሽከር የሆነ መንግሥት እንዲመሰረት እየሰሩ እንደሆነ መግለፃቸውን ኢፕድ ዘግቧል፡፡

ይህን ሁኔታ ሰላም ወዳድ የሆነ ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ሁሉ ሊኮንነው የሚገባ ሸውራራ አካሄድ መሆኑን አስታውቀዋል።