ም/ጠ/ሚ ደመቀ ህገወጥ የሰዎች ዝውውር ለመከላከል የደላሎችን ሰንሰለት መበጣጠስ ያስፈልጋል አሉ

ነሐሴ 12/2014 (ዋልታ) ህገወጥ የሰዎች ዝውውር ለመከላከል የደላሎችን ሰንሰለት መበጣጠስና የህግ ተጠያቂነትን ማስፈን እንደሚገባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በሰብሳቢነት የሚመሩት በሰው መነገድ፣ በህገወጥ መንገድ ድንበር ማሻገርና ለሥራ ወደ ሀገር ውጭ መላክ ወንጀሎች መከላከልና መቆጣጠር አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ዓመታዊ ስብሰባ ተካሂዷል።

በስብሰባው ማጠናቀቂያ በቀጣይ መከናወን ባለባቸው ጉዳዮች ላይ በሰጡት የሥራ መመሪያ ከኢትዮጵያ ወደ ተለያዩ አገራት በህገወጥ መንገድ ተሰደው የሚንገላቱ ዜጎች እንዳይኖሩ መከላከል ላይ ያተኮረ ሥራ ማከናወን ይገባል ብለዋል።

ሰፊ የማኅበረሰብ ንቅናቄ በመፍጠር ዜጎች እንዳይሰደዱ ማስተማር እንደሚገባ ጠቁመው ችግሩን በዘላቂነት ለፍታት የህገወጥ አዘዋዋሪ ወይም ደላሎችን ሰንሰለት መበጣጠስ እንደሚገባም ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ሰርቶ መለወጥና መልማት እንደሚቻል ማሳየት የደላሎችን ሰንሰለት በመበጣጠስ የህግ ተጠያቂነትን ማስፈን ቅድሚያ የሚሰጠው ትኩረት ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ለዚህ ደግሞ አዳዲስ መመሪያ ማውጣት ካስፈለገ ማውጣትን ጨምሮ የማያሰራ ህግን የማስተካከል ተግባር እንደሚከናወን ገልጸዋል።

በውጭ አገር በህገወጥ መንገድ የሚኖሩ ዜጎችን እንግልት መቀነስ የዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲያችን ማጠንጠኛ ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፋት ሁለት ዓመታት በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ዜጎች ወደ አገራቸው እንዲመለሱ መደረጉን ገልጸዋል።

በሳዑዲ አረቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ከማገኙ 100 ሺሕ አካባቢ ዜጎች ከ65 ሺሕ በላይ የሚሆኑት ወደ አገራቸው መመለሳቸውም የዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲው ውጤት ነው ብለዋል።

ከተመለሱ በኋላ ደግሞ ጊዜያዊ መጠለያ ከማዘጋጀት ባለፈ በቅብብሎሽ ወደ ትውልድ ቀያቸው ሄደው በዘላቂነት መቋቋም የሚችሉበት አሰራር በውጤት መታጀብ አለበት ብለዋል።

በልዩ ሁኔታ ከትግራይ ክልል ውጭ ያሉ ከስደት ተመላሾች እውቀታቸው፣ ልምዳቸውና ገንዘባቸውን ታሳቢ በማድረግ በዘላቂነት ማቋቋም እንደሚገባም አሳስበዋል።