ም/ጠ/ሚ ደመቀ ለኢትዮጵያ ክብርና ሉዓላዊነት የተዋደቁ ጀግኖችን አመሰገኑ

ግንቦት 2/2014 (ዋልታ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ለኢትዮጵያ ክብርና ሉዓላዊነት የተዋደቁ ጀግኖችን አመሰገኑ፡፡

የአማራ ክልል መንግሥት በሕግ ማስከበር እና በኅልውና ዘመቻው አስደናቂ ጀብዱ የፈጸሙ ጀግኖችን አመስግኗል፡፡

በምስጋና መርኃ-ግብሩ ላይ የተገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፤ ኢትዮጵያ ዛሬም ለክብሯና ለሉዓላዊነቷ ግንባራቸውን የሚሰጡ የግንባር ቀደሞች እናት መሆኗን ያስመሰከራችሁ ጀግኖች ናችሁ ብለዋቸዋል፡፡

በክህደት የተፈጸመብንን ወረራ ቀልብሰን፣ ታሪካዊ ጠላቶቻችንና በየጊዜው የጸረ ኢትዮጵያ አስተሳሰብን እየተጋረዱ የሚሰለፉት ኃይሎች ከከሃዲው ወራሪ ጋር ተባብረው የደቀኑብንን ኅልውና መክተን ለዚህ እንድንበቃ ላደረጉ ሁሉ ክብርና ምስጋና ይገባቸዋል ነው ያሉት፡፡

ኢትዮጵያ ከጥንት እስከ ዛሬ በተለያዩ አደጋዎችና ፈተናዎች ማለፏን ያስታወሱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና ክብር አስከብረን ተሻግረናል ብለዋል፡፡ ዋና አቅምና ታምዕራዊ ኃይል አብሮነት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የአጥፊው ኃይል ዋና ትኩረት አንድነታችንን ለማናጋት ያለመ ነውም ብለዋል፡፡ ከዚያም ከዚህም የሚወረወረውን ፀረ አንድነት አጀንዳ መመከት የጊዜው ዋና ትኩረትና ተግባር መሆን እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡

በብስለት፣ በተረጋጋና በሰላ አቅጣጫ መጓዝ ከምንጊዜውም በላይ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ ጊዜ እየጠበቁ የሚላኩትን ትርክቶችና አፍራሽ መልእክቶች እያመከኑና እየደፈቁ መራመድ ከሁሉም እንደሚጠበቅ አስገንዝበዋል፡፡

በሃይማኖት፣ በብሔርና አካባቢን መነሻ ያደረጉ መቃቃሮችንና ክፍተቶችን ለመፍጠር የሚደረጉ ቅስቀሳዎችንና ትንኮሳዎችን በአብሮነት ክንድ መመከት እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

በጸረ ኢትዮጵያ ዓላማ ናውዞ የነበረውን ኃይል ላስተነፈሱ፣ ኅልውናን ላረጋገጡና ለድል ላበቁ ሁሉ ምስጋናና ክብር ይገባቸዋል ነው ያሉት፡፡

ጀግናው የመከላከያ ሠራዊት የተፈጸመበትን ክህደት በመመከት ለፈጸመው ጀብዱ በታሪክ ሲዘከር እንደሚኖርም ተናግረዋል፡፡

እንደ አማራ ክልል ሁሉ የአፋር ክልል አናብስት የፈጸሙት ጀብዱና አስደናቂ ጀግንነት ሲዘከር እንደሚኖርም ተናግረዋል ሺል አሚኮ ዘግቧል፡፡

የተደቀነውን ወረራ ለመቀልበስ በተደረገው ርብርብ ኢትዮጵያውያን አንድ ሆነው ለሀገር የሚዋደቁ ጽኑ ሕዝቦች መሆናቸውን ያስመሰከሩበት መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

በተቀናጀ መንገድ የተከፈተውን ወረራ ለመቀልበስ በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውን ያደረጉት ዓለምን ያስደነቀ ርብርብ ለወዳጅም ለጠላትም ትምህርት የሰጠ መሆኑን አንስተው ለዲያስፖራ አባላትም ምስጋና አቅርበዋል፡፡