ም/ጠ/ሚ ደመቀ መኮንን ከአውሮፓ ኅብረት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ልዩ ተወካይ ጋር ተወያዩ

ግንቦት 10/2014 (ዋልታ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከአውሮፓ ኅብረት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ልዩ ተወካይ ጋር ተወያዩ፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ዛሬ በጽሕት ቤታቸው ከአውሮፓ ኅብረት የሰብአዊ ኮሚሽን ልዩ ተወካይ ኤመን ጊልሞር ጋር በሰብአዊ መብት ጉዳዮች ፣ በዕርዳታ ተደራሽነት እንዲሁም መንግሥት ሰላምን ለማረጋገጥ እየወሰዳቸው በሚገኙ እርምጃዎች ዙሪያ ውይይት አድርገዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ጊዜ በሰጡት ማብራሪያ የኢትዮጵያ መንግሥት ለዘላቂ ሰላም ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ተግባራዊ እርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑን ገልፀው በተቃራኒው የአሸባሪው ሕወሓት ቡድን ሌላ ዙር ጦርነት ለመክፈት ከፍተኛ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
እየቀጠለ ያለው የሕወሓት ትንኮሳ ሰብአዊ እና ቁሳዊ ውድመትን ከማስከተሉ በፊት ዓ ለም ዐቀፉ ማኅበረሰብ ሊያወግዘው እና ከፀብ ጫሪ ድርጊቱ እንዲታቀብ ግፊት እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
መንግሥት ከሕወሓት ጋር የነበረውን ጦርነት በተናጠል በማቆም ፣ እስረኞችን በመፍታት ፣ጦሩን ከትግራይ በማስወጣት እንዲሁም ያለተገደበ የሰብዊ እርዳታ ተደራሽ እንዲሆን እርምጃዎችን በመውሰድ ቁርጠኝነቱን አሳይቷል ብለዋል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡
ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በማዋቀር ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ እየተሰሩ ያሉ ሥራዎችም አብራርተዋል።
ሰብአዊ እርዳታ በጦርነት እና በድርቅ ተጎጂ ለሆኑ ማኅበረሰቦች ተደራሽ እንዲሆን መንግሥት ያልተቋረጠ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
ዓለም ዐቀፉ ማኅብረሰብ በጦርነት ተጎጂ ለሆኑ ለአፋር እና እና አማራ ክልል ሕዝቦችም እኩል ትኩረ መስጠት እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
የአውሮፓ ኅብረት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ልዪ ተወካይ ኤመር ጊሊሞር በበኩላቸው ኅብረቱ ከኢትዮጵያ ጋር ያለው ግንኙነት ለማሻሻል የሚያስችሉ ሥራዎች በሁለቱም ወገኖች እየተሰሩ መሆኑን አንስተዋል።
መንግሥት ያልተገደበ የሰብአዊ እርዳታ በጦር ቀጠና ላሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽ ለማድረግ የተኩስ አቁም ካደረገ በኋላ ያሉ ሁኔታዎች መሻሻላቸውን ገልፀው እርዳታን በበቂ ሁኔታ ለማድረስ ሁሉም አካል ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት ተናግረዋል።
በተጨማሪም በነበረው ጦርነት የሰብአዊ መብት ጥሰት እና ወንጀሎችን የፈፀሙ ተጠርጣሪዎች ተጠያቂ የማድረጉ ሂደት እንዲፋጠን ጠይቀዋል።