ሞዛምቢክ ለማላዊ ወደብ ለማከራየት ተስማማች

ነሐሴ 13/2016 (አዲስ ዋልታ) የደቡብ ምስራቅ አፍሪካዊቷ ሞዛምቢክ በሰሜኑ የሀገሪቷ ክፍል የሚገኘውን የናካላ ወደብ የባሕር በር ለሌላት ለጎረቤቷ ማላዊ ለማከራየት ተስማማች፡፡

ስምምነቱ የተደረገው በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን የንግድ ትስስር ለማጠናከር ሲሆን የሞዛምቢክ ፕሬዝዳንት ፊሊፔ ኒዩሲ እና የማላዊ አቻቸው ላዛሩስ ቻክዌራ የኪራይ ስምምነቱን ተፈራርመዋል፡፡

የናካላ ወደብ በማላዊ፣ ዛምቢያ እና ሞዛምቢክ በጋራ እየተገነባ የሚገኝ የናካላ የኮሪደር ልማት አካል ሲሆን የፕሮጀክቱ ዋና ዓላማ የቀጣናውን የልማት ትስስር ማጠናከርና የወደብ አገልግሎት ማመቻቸትን ያለመ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

የማላዊ ፕሬዝዳንት ላዛሩስ ቻክዌራ ስምምነቱ ሀገሪቷ በምድር ዕቃዎችን ለማጓጓዝ የምታወጣውን የነዳጅ ወጪ በእጅጉ የሚቀንስ በመሆኑ በተዘዋዋሪ በማላዊ የነዳጅ ዋጋ እንዲቀንስ የሚያደርግ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

የሞዛምቢክ ፕሬዝዳንት ፊሊፔ ኒዩሲም ስምምነቱ እንደ ሞዛምቢክ-ማላዊ የጋራ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ያሉ ታላላቅ ጅምር ፕሮጀክቶችን ያግዛል ማለታቸውን ዘ ማሪታይም ኤክስኪዩቲቭ ዘግቧል፡፡