ታኅሣሥ 27/2015 (ዋልታ) ሞዛምቢክ ለሁለት ዓመታት የሚያቆያትን በተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባልነት መቀመጫ አገኘች፡፡
አፍሪካዊቷ አገር አምስት ቋሚና አስር ተለዋጭ አባላት ባሉት ምክር ቤቱ ስትመረጥ ይህ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ ተነግሯል፡፡
ሞዛምቢክ ባለፈው አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር ሰኔ 2022 በሙሉ ድምጽ ለጸጥታው ምክር ቤት አባልነት የተመረጠች መሆኗም ተመላክቷል፡፡
በተባበሩት መንግስታት የሞዛምቢክ አምባሳደር ፔድሮ ኮሚሳሬዮ አፎንሶ ሞዛምቢክ ለመጀመሪያ ጊዜ የጸጥታው ምክር ቤት አባል ሆና መመረጧ ታሪካዊ ነው ብለዋል፡፡
አገራት ለጸጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባልነት ኮታ ጂኦግራፊያዊ ውክልናን መሰረት ያደረገ ቢሆንም ለአባልነት ለመወዳደር ረጅም ጊዜ የምረጡኝ ዘመቻ ማድርግ ይጠበቅባቸዋል፡፡
ኬንያ ከአፍሪካ የሁለት ዓመት አባልነት አገልግሎት ዘመን ያጠናቀቀችው ባለፈው ታኅሣሥ ወር ሲሆን ጋቦን እና ጋና ከ2022 ጀምሮ በምክር ቤቱ አባል አገራት መሆናቸውን የቪኦኤ ዘገባ አመላክቷል፡፡
አሜሪካ፣ ሩሲያ፣ ቻይና፣ እንግሊዝ እና ፈረንሳይ በተባበሩት መንግሥታት ጸጥታ ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ ያላቸው አገራት መሆናቸው ይታወቃል፡፡