ሠራዊቱ በሕዳሴ ግድብ ቀጣና አስተማማኝ ሰላም በማስፈን ግዳጁን እየፈፀመ እንደሚገኝ ተገለጸ

ሐምሌ 1/2014 (ዋልታ) ሠራዊቱ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ቀጣና አስተማማኝ ሰላም በማሰፈን ሌት ከቀን ግዳጁን እየፈፀመ እንደሚገኝ በምዕራብ ዕዝ የሜካናይዝድ ሞተራይዝድ ብርጌድ ዋና አዛዥ ኮሎኔል ንጋቱ አሰፋ ገለፁ።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ያለአንዳች የፀጥታ ችግር ግንባታው እየተከናወነ መሆኑን የገለፁት ኮሎኔል ንጋቱ ሠራዊቱ በቀጣናው አስተማማኝ ሰላም ለማስፈን ግዳጁን ቀን ከሌት በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ብርጌዱ በሕዳሴው ግድብ ሊቃጣ የሚችል ማንኛውንም አይነት ጥቃት ለመቀልበስ በሚያስችል ቁመና ላይ መሆኑንም ተናግረዋል።

የክፍለ ጦሩ መቺ ኃይል የሆነው ብርጌዱ በተሰለፈባቸው አውደ ውጊያዎች አንፀባራቂ ገድል በመፈፀም ሕዝብ እና መንግሥት ያኮራ ተግባር መፈፀም መቻሉን ያስታወሱት ኮሎኔል ንጋቱ በቀጣይም ጥንካሬውን ይዞ የሚቀጥልበትን አቅም ፈጥሯል ብለዋል።

የብርጌዱ ምክትል አዛዥ ሌ/ኮ ሽፈራው ታያቸው በበኩላቸው ጠላት ቀጣናውን ለማተራመስ በቅጥረኛ ተላላኪ ኃይሎች አማካኝነት በተደጋጋሚ ትንኮሳ ቢሞክርም የሞተራይዝድ ብርጌዱ ከሌሎች የፀጥታ ኃይሎች ጋር በመቀናጀት አይቀጡ ቅጣት ቀጥቶ ሰላም ማስፈን መቻሉን ገልፀዋል።

በቀጣናው የተሰማራው የሜካናይዝድ ብርጌድ ሊፈጠር ለሚችልን የፀጥታ ስጋትን በአስተማማኝ ለመመከት በተጠንቀቅ ሆኖ ግዳጁን በመፈፀም ላይ እንደሚገኝም አዛዦቹ ማረጋገጣቸውን ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ፌስቡክ ገፅ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW