ሩሲያ ህወሓት በዓለም የምግብ ፕሮግራም መጋዘን የፈጸመውን የነዳጅ ዝርፊያ አወገዘች

አምባሳደር ኢቭጌኒ ተረክሂን

ነሐሴ 19/2014 (ዋልታ) ህወሓት በዓለም ምግብ ፕሮግራም መጋዘን ውስጥ የነበረ 570 ሺሕ ሊትር ነዳጅ መዝረፉ አስነዋሪና ተቀባይነት የሌለው ተግባር መሆኑን በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኢቭጌኒ ተረክሂን ተናገሩ።

በመቀሌ በሚገኘው የዓለም ምግብ ፕሮግራም መጋዘን ውስጥ የነበረ 12 ታንከር ወይም 570 ሺሕ ሊትር ነዳጅ በህወሓት መዘረፉን የተባበሩት መንግሥታት ቃል አቀባይ ስቴፈን ዱጃሪክ መግለጻቸው ይታወቃል።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር ዴቪድ ቤስሌይ ህወሓት የዘረፈውን ነዳጅ በአፋጣኝ እንዲመልስ የጠየቁ ሲሆን በነዳጁ መዘረፍ ምክንያት የሰብዓዊ እርዳታዎችን ለማሳለጥ እንቸገራለን ብለዋል።

በዚህ ዙሪያ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኢቭጌኒ ተረክሂን በመጋዘኑ ውስጥ የነበረው የምግብና የነዳጅ ክምችት በአስችጋሪ ሁኔታ ለነበሩ ዜጎች ሰብዓዊ ድጋፍ የሚውል እንደነበር ጠቅሰዋል።

በሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ችግር ሰለባ ለሆኑ የትግራይ ማኅበረሰብ መድረስ የነበረበት እርዳታ በሽብር ቡድኑ መዘረፉ ተቀባይነት የሌለውና አስነዋሪ ተግባር ነው ብለዋል።

ዘራፊዎቹ ነውረኛ ድረጊታቸውን ክደው ከተወሰነ ጊዜ በኋላ የትግራይ ሕዝብ ለችግር ተዳርጓል የሚል የተለመደ ልፈፋቸውን እንደሚቀጥሉና የሕዝብ ተቆርቋሪ ለመምሰል እንደሚሞክሩም ነው የገለጹት።

በህወሓት የሽብር ቡድን የተፈጸመውን ዝርፊያ የትኛውም የዓለም ማኅበረሰብ የማይደግፈው ድርጊት ነው ብለዋል።

የተፈጸመውን ድርጊት ማውገዝ እንደሚገባ ጠቅሰው አንዳንድ ድርጊቱን በዝምታ የሚያልፉ  አካላትም እውነታው በገሃድ መውጣቱ እንደማይቀር ማወቅ አለባቸው ነው ያሉት።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW