ሩሲያ እና ቻይና በአይነቱ የተለየ የጋራ የጦር ልምምድ ማካሄድ ጀመሩ


ነሃሴ 05/2013 (ዋልታ) –
ሩሲያ እና ቻይና በአይነቱ የተለየ የተባለለትን የጋራ የጦር ልምምድ በሰሜናዊ ቻይና ማካሄድ ጀመሩ፡፡
የሁለቱ ሀገራት የጦር ልምምድ አሜሪካንና ምዕራባዊያን ሀገራትን አስደንግጧል ሲል አልጀዚራ ዘግቧል።
የሩስያ መከላከያ ሚኒስቴር ዛሬ እንዳስታወቀው ሞስኮ ለዚህ በዓየነቱ ልዩ ለሆነው የጋራ ወታደራዊ ልምምድ በርካታ ተዋጊ ሂሊኮፕተሮችን፣ የዓየር መከላከያ ሲስተም እና ሌሎች ዓለም የደረሰችባቸውን የጦር መሳርያዎችን ወደ ልምምድ ሥፍራው መላኳን ይፋ አድርጓል።
ቻይና እና ሩስያ ከምዕራባውያን ለሚቃጣባቸው ማንኛውም ዓይነት ጥቃት ዝግጁነታቸውን ለመግለጽ የታሰበ ነው በተባለለት በዚህ የጋራ ልምምድ ከሁለቱም ሀገራት ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሠራዊት መሳተፉ ነው የተገለጸው፡፡
በተጨማሪም ልምምዱ ቀጠናዊ ሽብርተኝነትን ለማጥፋት ያለመ ነው ተብሏል፡፡
የሁለቱ ሀገራት የጋራ ጦር ልምምድ ሰኞ እለት የጀመረ ሲሆን እስከ ፊታችን አርብ ይቀጥላል ነው የተባለው፡፡
በጦር ልምምዱ ከ10 ሺህ በላይ እግረኛ ጦር እና አየር ሀይል እየተሳተፈ ነው፡፡
“በደቡባዊ ቻይና ባህር” ውዝግብ ዙርያ አሜሪካ የምታደርገው ጣልቃ ገብነት መታገስ ከምትችለው በላይ መድረሷን የምትገልጸው ቻይና ፤ ዋሽንግተንን የደቡባዊ ቻይና ባህር ሠላም እና ደህንነት ጠንቅ ስትል ፈርጃታለች።
ቻይና እና ሩሲያ አሜሪካ በተደጋጋሚ በሀገራት ጉዳይ የምታደርገውን ጣልቃገብነት እንድታቆም ሲያስጠነቅቁ መቆየታቸው የሚታወስ ነው፡፡
ቻይና አሜሪካ በታይዋን ጉዳይ የምታደርገውን ጣልቃገብነት ካላቆመች ቻይና ትምህርት ልትሰጣት ዝግጁ ናት ማለቷ የሚታወስ ነው፡፡