ጥር 15/2015 (ዋልታ) ሩሲያ የኢስቶኒያ አምባሳደር ማርጉስ ሌድሪ በሁለት ሳምንት ውስጥ ሀገሯን ለቀው እንዲውጡ ትእዛዝ ሰጠች፡፡
የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ ሩሲያ በአንድ የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገር ላይ እንዲህ አይነት እርምጃ ስትወስድ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው፡፡
ሩሲያ በዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰችው ኢስቶኒያ በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ በዋና ከተማዋ ታሊን የሩሲያ ኤምባሲ ዲፕሎማቶችን እና የአስተዳደር ሰራተኞችን ቁጥር መቀነሷን ተከትሎ ነው ተብሏል፡፡
ኢስቶኒያ በሀገሯ የሚገኘው የሩሲያ ኤምባሲ በስምንት ዲፕሎማቶች እና 15 የአስተዳደር ሰራተኞች ብቻ እንዲመራ ውሳኔ ማስተላለፏ ይታወሳል፡፡
ውሳኔውን ተከትሎ የሁለቱ ሀገራት ግንኙት በጉዳይ አስፈፃሚ (charges d’affaires) እንዲመራ ሩሲያ ውሳኔ ያስተላለፈች ሲሆን ኢስቶኒያም ተመሳሳይ እርምጃ እንደምትወስድ ማስታወቋን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡