ሩሲያ 10 የአሜሪካ ዲፕሎማቶችን አባረረች

ሩሲያ 10 የአሜሪካ ዲፕሎማቶችን አባረረች

ሚያዝያ 09/2013 (ዋልታ) – ሩሲያ 10 የአሜሪካ ዲፕሎማቶችን ያባረረች ሲሆን፣ ሌሎች ስምንት ከፍተኛ የአሜሪካ ባለሥልጣናት ደግሞ ወደ አገሯ እንዳይገቡ ጥቁር መዝገብ ውስጥ ማስገባቷ ተገለፀ።

ሩሲያ ይህን ያደረገችው ማክሰኞ ዕለት አሜሪካ ለጣለችባት ማዕቀብ አፀፋዊ ምላሽ ነው ተብሏል።

በመሆኑም የአሜሪካ ፌደራል ፖሊስ (ኤፍቢአይ) አባላትና የአሜሪካ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ባለሥልጣናት ወደ ሩሲያ እንዳይገቡ ታግደዋል።

በዋይት ሐውስ ሩሲያ ላይ የተጣለው ማዕቀብ ባለፈው ዓመት በነበረው ‘የሶላር ዊንድ’ የሳይበር ጠለፋ እና ሌሎች “ጠብ አጫሪ” ድርጊቶች እንዲሁም በ2020 ምርጫ ጣልቃ ገብነቷ ምላሽ እንደሆነ አስታውቋል።

ይህንን ተከትሎ በከፍተኛ ሁኔታ ቅራኔ ውስጥ የገቡት ሁለቱ አገራት፣ አሁን ደግሞ ወደ ባሰበት ውጥረት ውስጥ እየገቡ ነው።

ሩሲያ በሺህዎች የሚቆጠሩ ወታደሮቿን ወደ ዩክሬን ያስጠጋች ሲሆን፣ የአሜሪካ የጦር መርከቦችም ወደ ጥቁር ባሕር እያመሩ መሆኑን የሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስጠንቅቋል።

ባለፈው ወር መንግሥትን በሚተቸው አሌክሲ ናቫንሊይ መመረዝ ምክንያት አሜሪካ ሰባት የሩሲያ ባለሥልጣናትን እና በርካታ የመንግሥት ተቋማትን ኢላማ አድርጋለች። ሩሲያ ግን በአሌክሲ መመረዝ እጇ እንደሌለበት ገልጻለች።

ሆኖም በዚህ ሳምንት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ለሩሲያ አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን ሁለቱ አገራት አብረው ሊሰሩባቸው የሚችሉባቸው ሁኔታዎች እንዲመቻቹ ጥሪ አቅርበዋል።

ሩሲያም ይህንን በበጎ እንደምትመለከተውና እያሰበችበት እንደሆነ መግለጿን አስታውሶ ቢቢሲ ዘግቧል።