ሩስያ 20 የቼክ ሪፐብሊክ ዲፕሎማቶችን አባረረች

ሚያዝያ 11/2013 (ዋልታ) – ቼክ ሪፐብሊክ ባለፈው ቅዳሜ 18 የሩስያ ዲፕሎማቶችን ማባረሯን ተከትሎ ሩሲያ በአጸፋው 20 የቼክ ሪፐብሊክ ዲፕሎማቶችን አባረርች።

የቼክ ደህንነት ሰዎች እንደሚሉት የተባረሩት ሩስያዊያን ዲፕሎማቶች በድብቅ የስለላ ሥራ የሚሠሩ ናቸው።

ቼክ ሪፐብሊክ ሰዎቹን ያባረረቻቸው በፈረንጆቹ 2014 በአንድ የጦር መሣሪያ ማከማቻ ዴፖ ላይ በደረሰ ፍንዳታ ላይ እጃቸው አለበት በሚል ነው።

የአውሮፓ ሕብረት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ሰኞ ዕለት ስለ ጉዳዩ እንደሚመክሩ ተነግሯል።

ሩስያ የቼክ ሪብሊክ ዲፕሎማቶች በአንድ ቀን ሞስኮን ጥለው እንዲወጡ ያዘዘች ሲሆን፣ ቼክ ሪፐብሊክ ደግሞ 72 ሰዓታት ሰጥታለች።

የሩስያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የቼክን ውሳኔ “ያልተጠበቀ” እንዲሁም “ጠብ አጫሪ” ብሎታል።

ሚኒስቴሩ ባወጣው መግለጫ “በቅርቡ ሩስያ ላይ የተጣለውን ማዕቀብ ተከትሎ ዩናይትድ ስቴትስን ለማስደሰት ካላቸው ፍላጎት አንፃር ነው የቼክ ባለሥልጣናት ይህን ድርጊት የፈፀሙት” ብሏል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።