“ሪፎርሞቻችንን አጠናክረን እናስቀጥላለን፤ የህዝባችንን ተጠቃሚነት ከሙሉ ተሳትፎው ጋር እናረጋግጣለን” – ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ

ጳጉሜን 2/2016 (አዲስ ዋልታ) ሪፎርሞቻችንን አጠናክረን እናስቀጥላለን፤ የህዝባችንን ተጠቃሚነት ከሙሉ ተሳትፎው ጋር እናረጋግጣለን ሲሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ።

ርዕሰ መስተዳድሩ የዛሬውን የጳጉሜን – የሪፎርም ቀን አስመልክቶ ያስተላለፉት መልዕክት እንደሚከተለው ቀርቧል፦

“ሪፎርም ለላቀ አገልግሎት”

“ሪፎርሞቻችንን አጠናክረን እናስቀጥላለን፤ የህዝባችንን ተጠቃሚነት ከሙሉ ተሳትፎው ጋር እናረጋግጣለን”

በሀገራችን የለውጥ ብርሃን ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የአጠቃላይ ዜጎችን የባለቤትነት፣ ተሳታፊነትና በሂደቱም ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ታሳቢ ያደረጉ በርካታ ሪፎርሞች ተተግብረዋል፡፡ በክልላችንም በተለያዩ የሪፎርም ስራዎች የህዝባችንን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ብዙ ተግባራት ተከውነዋል፡፡

በአማራ ክልል ከለውጥ በፊት በብዛት፣ በጥራትና በፍትሃዊነት ሚዛን ከተገቢዉ ልኬት ያነሱ የነበሩ የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች ምላሽ ማግኘት የጀመሩ ሲሆን የመንገድ ዘርፍ ስራዎችና የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚነት ላይ ያየናቸው ለውጦች መልካምና ተጠናክረው እንዲቀጥሉ በትኩረት የምንሰራባቸው ዘርፎች ናቸው፡፡

ክልላችን ያሉትን ሰፋፊ የልማት አቅሞች ተጠቅሞ በኢንዱስትሪዉ ዘርፍ የነበረውን ክፍተት የሚያክሙ ስራዎች በመሰራት ላይ ይገኛሉ፡፡ በርካታ አምራች ኢንዱስትሪዎች በግንባታና ላይ ሲሆኑ ማምረት ላይ የሚገኙትም ቀላል አይደሉም፡፡ ከእንዚህ አምራች ኢንዱስትሪዎች መካከል የሚገኘው ግዙፉ የለሚ ናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካ በክልላችን ተገንብቶ ወደ ምርት ለመግባት በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡ ይህ ፋብሪካ በሙሉ አቅሙ ማምረት ሲጀምር ለዜጎች ከሚፈጥረው ሰፊ የስራ እድል በተጨማሪ ከፍ ያለ የኮንስትራክሽን ዘርፍ መነቃቃት ይፈጥራል፡፡

የኢኮኖሚያችን ወሳኝ ክፍል የሆነውን ግብርና ለማዘመን የጀመርናቸውን ስራዎች የሚሸከምና ውጤት የሚያመጣ የግብርና ተቋም ሪፎርም እየተሰራ ሲሆን በሌላም በኩል ፀጋው እያለን ሳንጠቀምበት የቆየውን የማዕድን ልማት ዘርፍ ወደ ስራ ገብቶ ጅምር ውጤቶችንም ማሳየት ጀምሯል፤ ይህም በከፍተኛ ትኩረትና ንቃት የሚመራ ይሆናል፡፡

ክልላችን በማዕድን ዘርፍ ያለው ከፍ ያለ እምቅ አቅም መሆኑም ሀብቱን በአግባቡ አልምተን ክልላችንን እና ሀገራችንን የምንጠቅምበት ይሆናል፡፡ በቱሪዝም ዘርፉም ክልላችን የታሪካዊ፣ ባህላዊ፣ ኃይማኖታዊና ተፈጥሯዊ የቱሪዝም ሀብቶች ባለቤት ነው፡፡ ቱሪዝም በባህሪው ከሁሉም በተለየ ሰላምን አብዝቶ የሚፈልግ ዘርፍ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ የታየበትን መቀዛቀዝም ጭምር የሚያካክስ ስራን መስራት ይጠበቅብናል፡፡ በጥቅሉ በየኢኮኖሚ ዘርፉ የክልላችንን እምቅ አቅሞች ለይተን በተሻሻለ አሰራርና በትብብር ውጤት ለማስመዝገብ እንረባረባለን፡፡

በለውጡ ምዕራፍ ውስጥ የጀመርነውና በምርጫ የህዝባችንን አደራ ተቀብለን በቀጠልንበት ወቅት ለማሻሻል ስራዎች እየሰራንበት የምንገኘው የፀጥታና ፍትህ ተቋማት ላይ የሚሰራው ስራ ነው፡፡ የዲሞክራሲን ምህዳር የማስፋት እና ጎን ለጎንም የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ በከፍተኛ ትኩረት በመስራት ላይ የምንገኝ ሲሆን በክልላችን ያጋጠመውን የስርዓት አልበኝነት እንቅስቃሴ በህዝባችንና በህዝብ መገልገያ ተቋማት ላይ ያደረሰውን ጥፋት የማንረሳው ጠባሳ ቢሆንም ዳግም በማይታሰብበት መልኩ በመሰረታዊነት ሁኔታውን ለመቀየር እየሰራን እንገኛለን፡፡ ለዚህ ተግባር ውጤታማነትም የህዝባችን ትብብር እና ሰላሙን ከመንግስት ጋር ተቀናጅቶ ለማስጠበቅ በትጋት እየሰራ ይገኛል፡፡ አጥፊዎችን እየለዩ ተጠያቂ ማድረግ፣ የንፁሃን ዜጎችን ደህንነት ማረጋገጥ ላይ ለምንሰራቸው ስራዎች አሁንም የህዝባችንን የነቃ ተሳትፎ የምንፈልግ ሲሆን በፀጥታና ፍትህ ተቋማት ላይ የጀመርናቸውን ሪፎርሞች በዘላቂነት ችግርን በሚፈታ አግባብ ለማጠናቀቅ እንደምናስቀጥላቸውም ላረጋገጥ እወዳለሁ፡፡

ሌላው ከፍተኛ የሆነ ሪፎርም የተደረገበት የሀሳብ ነፃነትና የሚዲያ ጉዳይ ነው፡፡ በሀገራችን እና በክልላችን ሰዎች በያዙት ሃሳብ ምክንያት ይደረግባቸው የነበረ መፈረጅ፣ መሳደድና ስቃይ እንዲያበቃ በእጅጉ ተሰርቷል፡፡ እኛ ሁሌም ለሀሳብ ነፃነትና ለሀሳብ ተደማሪነት ቦታ አለን፡፡ የሀሳብ ማስተላለፊያና የአዳዲስ እይታዎች ለገበያ መቅረቢያ ለሆኑት ሚዲያዎች ነጻነትም አበክረን እንሰራለን፡፡

በክልላችን የገጠመን ችግር ግን ከዚህ የሚቃረን ሆኖ ቆይቷል፡፡ በሀሳብ ሜዳ የተሸነፉና ዘላቂ አማራጭ ሀሳብ የሌላቸው፣ የቀንና ሌት ስራቸውን የሌሎችን ስም በማጉደፍና ሀሳብን በሀይል ማፈን የሚችሉ በመሰላቸው፣ የሚዲያን የሀሳብ ገበያ ሜዳነት አብዝተው የሚክዱና ሀሳብ የሚፈሩ፣ ጋዜጠኞችን በማፈን ሳይቀር ሀሳብን ማሸነፍ የሚችሉ በመሰላቸው፣ በማህበራዊ ሚዲያ ወጥተው ህዝብን አወናባጅና ሀሰተኛ ወሬዎችን ሲረጩ መዋልን ልምምዳቸው ያደረጉ አካላት ራሳቸውን በሰላም ቦታ አስቀምጠው ወገናቸውን ሰላም በሚነሳ መንገድ ሲንቀሳቀሱ ቆይተዋል፡፡

ዛሬም ሆነ ነገ ሀሳብ ኖሮት በሀሳብ ለሚሞግትም ለሚወዳደርም ክብር ያለን ብቻም ሳንሆን ከተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች ውስጥ በክልላችን ካቢኔ ውስጥ እድል ሰጥተንና ተባብረን ህዝባችንን እያገለገልን እንገኛለን፡፡ በዚህ አጋጣሚ ለተወደደው ህዝብ ያለኝ አደራ ነገርን ከስሩ ዉሃን ከጥሩ ነውና ነገሩ በጫፍ ይዞ አራጋቢዎችና በነጭ ውሸት አምራቾች ሳይታወክ ለሰላሙና ልማቱ በትብብር እንዲቆም ነው፡፡

በመንግስት አገልግልት አሰጣጡ ማህበረሰባችን በሙስና እና በብልሹ አሰራር እንዳይማረር ተቋማቶቻችን ከሰው ሀይላቸው ከስራ ቦታቸው እንዲሁም ከወረቀት ንክኪ ወደ ዲጂታል አገልግሎት እንዲሸጋገር በ2016 በጀት ዓመት ሪፎርም ማድረግ ተጀምሯል፡፡ ይህንንም አጠናክረን የምናስቀጥለው ይሆናል። በስራዎቻችን ሁሉ ግልጽነትንና ተጠያቂነትን ለማስፈን፣ የህዝብን ተጠቃሚነት እና ብልፅግና ዕውን ለማድረግ ሪፎርም የማይተካ የሁለተናዊ መዳረሻችን  ምሰሶ ነው።

የሪፎርም ስራን አጠናክረን የምንቀጥለው ካለፈው የምንወስዳቸውን መልካም ወረቶች ሁሉ አጠናክረን ለመቀጠልና ችግሮችን እየፈታን የወቅቱን ፍላጎችና እርምጃዎች የሚረዱ፣ የሚያሳልጡና ህዝብን የሚጠቅሙ ተቋማት ግንባታዎቻችን ዕውን ለማድረግና የምናልመውን ሁለንታናዊ ብልፅግና ለማሳካት ነው፡፡

ሪፎርሞቻችንን አጠናክረን እናስቀጥላለን፤ የህዝባችንን ተጠቃሚነት ከሙሉ ተሳትፎው ጋር እናረጋግጣለን!