ርዕሰ መስተዳድሩ የአርሶ አደሮቻችን ጥንካሬ የሀገር ልማት መሠረት ነው አሉ

ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር)

መጋቢት 3/2015 (ዋልታ) የአርሶ አደሮቻችን ጥንካሬ የሀገር ልማት መሠረት ነው ሲሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በደቡብ ጎንደር ዞን ሊቦከምከም ወረዳ እየተሠራ የሚገኘውን የተቀናጀ ማኅበረሰብ አቀፍ ልማት ጎብኝተዋል፡፡

የልማት ፕሮጀክቱ በአመልድ ኢትዮጵያ እና ግሊመር ፋውንዴሽን በተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት የሚከናወን መሆኑ ተገልጿል፡፡

የፕሮጀክቱ አንዱ አካል የሆነው የጭብርና አነስተኛ መስኖ አውታር ግንባታ በዛሬው ዕለት የተመረቀ ሲሆን ፕሮጀክቱ በአንድ ዙር ብቻ 66 ሄክታር መሬት ማልማት ይችላል ተብሏል።

ርዕሰ መስተዳድሩ ዛሬ የተመረቀው የመስኖ አውታር እና ሌሎች በመሠራት ላይ ያሉ ፕሮጀክቶች የአርሶ አደሮችን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል አይነተኛ ሚና አላቸው ብለዋል።

መሰል አነስተኛ የመስኖ አውታሮችን በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በመሥራት የመስኖ ልማት እንዲጠናከር በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል።

“የአርሶ አደሮቻችን ጥንካሬ የሀገር ልማት መሠረት ነው” ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ አርሶ አደሮች ከክረምት እርሻ በተጨማሪ በመስኖ ልማት ላይ ጠንክረው መሥራት እንዳለባቸው ጥሪ አቅርበዋል።

በጭብርና አነስተኛ የመስኖ አውታር ምርቃት ላይ የተገኙ የግናዛ ቀበሌ አርሶ አደሮች በፕሮጀክቱ በዓመት ሦስት ጊዜ የማምረት እድል እንደተፈጠረላቸው ተናግረዋል፡፡

ከአመልድ ኢትዮጵያ የሚያገኙትን አነስተኛ ብድር በመጠቀም በእንስሳት ሃብት ልማት እና በሌሎች የሥራ ዘርፎች ላይ ተሰማርተው ኑሯቸውን እያሻሻሉ እንደሚገኙ መጠቆማቸውንም አሚኮ ዘግቧል፡፡