ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ በሶማሌ ክልል የተከሰተው ድርቅ እስከ ሚያዚያ ሊቀጥል እንደሚችል ገለጹ

ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ

የካቲት 1/2014 (ዋልታ) በሶማሌ ክልል የተከሰተው ድርቅ እስከ ሚያዚያ ድረስ ሊቀጥል እንደሚችል የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሀመድ አስታወቁ፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ ከሌሎች የክልሉ መንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመሆን ከዩኤስኤይድ ኢትዮጵያ ዳይሬክተር ሴን ጆንስ ጋር በክልሉ በተከሰተው ድርቅ ሁኔታ ላይ መክረዋል፡፡

በውይይታቸውም በክልሉ የድርቁ ሁኔታ እስከ ሚያዚያ ድረስ ሊቀጥል ይችላል ነው ያሉት።

የክልሉ መንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በድርቁ የተጎዱ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ከምግብ እጥረት አደጋዎች ለመከላከል ሥራዎች በመሠራት ላይ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም ለእንስሳት መኖ በማቅረብ ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

የዩኤስኤይድ ኢትዮጵያ ዳይሬክተር ሴን ጆንስ በበኩላቸው ድርጅታቸው በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች አስቸኳይ የሰብኣዊ ድጋፍ ለማድረግ በቁርጠኝነት ይሰራል ማለታቸውን ከክልሉ መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።