ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ በክልሉ በዘንድሮው ዓመት 1.2 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ለውጭ ገበያ ይቀርባል አሉ

የካቲት 06/2015 (ዋልታ) – የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ በዘንድሮው ዓመት ከክልሉ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ለውጭ ገበያ እንደሚቀርብ ገለጹ፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ኢትዮጵያ ስንዴን ወደ ውጭ መላክ መጀመሯ የሀገሪቷ ብልጽግና ጉዞ ጅምር ማሳያ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ለዚህ ስኬት የተጉ ጠንካራ የሀገሪቱ አርሶ አደሮችን እና የልማት አጋሮችንም አመስግነዋል፡፡

ኢትዮጵያ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ስንዴን ወደ ውጭ ለመላክ የማስጀመሪያ መርኃ ግብር በኦሮሚያ ክልል ባሌ ዞን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት በይፋ አስጀምራለች።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማክሮ ኢኮኖሚ አማካሪና የስንዴ ኤክስፖርት ብሔራዊ ኮሚቴ አስተባባሪ አምባሳደር ግርማ ብሩ ሀገሪቱ በዓመት ከአገር ውስጥ ፍጆታ የሚተርፍን ከ32 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ስንዴ ወደ ውጭ የመላክ አቅም እንዳላት ተናግረዋል፡፡