ርዕሰ መስተዳድር እርስቱ ይርዳው ለደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት አስተላለፉ

                                                                     ርዕሰ መስተዳድር እርስቱ ይርዳው

ኅዳር 14/2014 (ዋልታ) የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እርስቱ ይርዳው በይፋ የተመሰረተውን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት በማስመልከት የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት አስተላለፉ፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ ምንም እንኳን አሁን የምንገኝበት ወቅት ሀገርን ለማዳን ከፍተኛ ተጋድሎ የምናደርግበት ጊዜ ቢሆንም አዲስ የተመሰረተው ክልል ለኅልውና ዘመቻው ተጨማሪ አቅም ነው ብለዋል።

የሁለቱም ክልል ህዝቦች ከዚህ ቀደም ለኅልውና ዘመቻው እያደረጉት ያለውን ጥረት በማስቀጠል የጋራ ጠላታችንን እንዲፋለሙ ጥሪ አቅርበዋል።

ከክልሉ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ አንዳመላከተው የሁለቱ ክልል ህዝቦች የጋራ ማንነት እና እሴት ባለቤት መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡

ለመንግስታዊ አገልግሎት የተዋቀረው አስተዳደራዊ መዋቅር አንድነታችንን ከማጠናከር አያግደንም ሲሉ ነው በመልዕክት ያስተላለፉት፡፡

አዲሱ ክልል እንዲመሰረት የነባሩ ክልል መንግስት አበክሮ ሲሰራ መቆየቱን የተናገሩት ርዕሰ መስተዳድሩ በቀጣይም የህዝቦችን ወንድማማችነት እና አብሮነት በማጠናከር የህብረተሰቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ እንደሚሰራም አስረድተዋል።