ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ የብልጽግና ፓርቲ ጉባኤ አካታችና ሁሉም ኢትዮጵያዊያን የተሳተፉበት ነው አሉ

መጋቢት 7/2014 (ዋልታ) የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ የብልፅግና ፓርቲ ጉባኤ አካታች፣ ሁሉን ዐቀፍ እንዲሁም ሁሉም ኢትዮጵያዊያን የተሳተፉበት መሆኑን ገለጹ፡፡
የፓርቲው መጀመሪያ ጉባኤን የግልፅነትና ፍፁም የዴሞክራሲያዊ አሰራርና መርህን የተከተለ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች በልካቸው ውክልና ያገኙበት መሆኑም ልዩ እንደሚያደርገው ተናግረዋል።
ጉባኤው በተለያዩ አጀንዳዎች መምከሩን ያስታወሱት ርዕሰ መስተዳድሩ በተለይም በጉባኤው የተላለፉ ውሳኔዎችና አቅጣጫዎችም ኅብረተሰቡ የሚያነሳቸው ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት የሚያስችሉ ናቸው ብለዋል፡፡
ፓርቲው ያሳለፋቸው ውሳኔዎች ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍና የተገኙ ውጤቶችን በማጠናከር ለመጪው ትውልድ ምቹ ሁኔታን መፍጠር የሚያስችሉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በጉባኤው ከተቀመጡ አቅጣጫዎች መካከል አመራርና አባላትን የማጥራት ሥራ አንዱ መሆኑን ጠቁመው ከዚህ አንፃርም በክልሉ እየተከናወኑ ያሉ ጅምር ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል፡፡
ሰላምና ደኅንነትን ለማረጋገጥ እየተከናወኑ የሚገኙ ሥራዎችን ማጎልበት ሌላው ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ መሆኑን አመላክተው በተለይ የፀጥታ ኃይሎች ከብሔር፣ ፓርቲና ከሃይማኖት ወገንተኝነት ነፃ በሆነ መልኩ ሁሉንም ዜጋ በእኩልነት እንዲያገለግሉ የማስቻል ሥራ በትኩረት እንደሚሰራ አንስተዋል፡፡
ከክልሉ ነባራዊ ሁኔታ ጋር ተያይዞም በክልሉ ለሚገኙ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር እና የማምረቻ ስፍራዎች ማዘጋጀት ልዩ ትኩረት እንደሚሰጥ ያብራሩት ርዕሰ መስተዳድሩ በክልሉ በፕሮጀክቶች አፈፃፀም የሚታዩ ችግሮን እንዲቀረፉም ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል ብለዋል፡፡
ኅብረተሰቡም ፓርቲው እያከናወናቸው ባሉ ተግባራት ድጋፉን እንዲያጠናክ ጥሪ ማቅረባቸውን ከክልሉ መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን የተገኘው መረጃ አመላክቷል፡፡