ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል የአማራና ኦሮሚያ ክልል አመራሮች የሚከሰቱ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት እየሰራ መሆኑን ገለጹ

መጋቢት 14/2014 (ዋልታ) የአማራና ኦሮሚያ ክልል አመራሮች የሚከሰቱ ችግሮችን የሕዝብ መፈናቀሎችን ለመፍታት እየሰራ መሆኑን የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) ገለጹ።
የኦሮሚያ ክልል አመራሮች የሚፈናቀሉ ዜጎችን ችግር ለመቅረፍና በጥናት በመለየት ወደ ቀያቸው ለመመለስ እየሰሩ እንደሆነና አመራሩንም መደገፍና ማበረታታት እንደሚገባ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በምጣኔሃብት፣ ፀጥታ እና ፖለቲካ ታማለች ያሉት ርዕሠ መስተዳድሩ ለዚህ ፈውስ ደግሞ በጋራ መቆም እንደሚገባና አገር ለማፍረስ እንቀሳቀሳለሁ ያለውን በጋራ መታገል እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በባሕር ዳር ከተማ በተካሄደው የሕዝብ የውይይት ከተሳታፊዎች ለተነሱላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ማብራሪያ እንደ አማራ ክልል አሸባሪ ትሕነግን ለመቀልበስ በተደረገው ጥረት ሁሉም በየአደረጃጀቱ ዋጋ ከፍሏል፤ ደሙን አፍሷል፤ ህይወቱን መስዋእት አድርጓል ነው ያሉት።
ለዚህ ደግሞ ፋኖም ከመከላከያ ሠራዊቱ፣ ከልዩ ኃይሉና ከሚሊሻው ጋር ዋጋ ከፍሏል ለዚህም ትልቅ አድናቆት አለን ብለዋል።
ለፋኖ፤ ለልዩ ኃይልና ለሚሊሻው በምንሰጠው እውቅና ልክ እውቅና እንሰጣለን ሲሉም ተናግረዋል።
ነገር ግን በፋኖ ስም ዘረፋ፣ ማሸበር እና ህገወጥ አደረጃጀት እየፈጠሩ የሕዝቡን ሰላም የሚነሱና በፋኖ ስም የሚነግዱ መኖራቸውን ጠቅሰው እነዚህን ወደ ህግና ሥርዓት ለመመለስ ክልሉ የሚሰራውን ሥራ ሕዝቡም ሊደግፈን ይገባል ብለዋል።
የኑሮ ውድነትን ለማቃለል ተጨማሪ ምርት ማምረትና የቁጠባ ባህላችንን ማሳደግ ይገባል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ እንደሀገር ችግሩን ለመወጣት ተደጋግፈን ማለፍ አለብንም ነው ያሉት።
አመራሩ የሚሰራውን ሥራ በማረምና በመደገፍ፣ ችግሮችን እንዲያርም በማድረግ የክልሉ ሕዝብ ሰላምና ልማት እንዲያገኝ ማድረግ ከሕዝቡ ይጠበቃልም ሲሉ አክለዋል።
ርዕሠ መስተዳድሩ የአማራ ክልል ምጣኔሃብታዊ ችግር የሚፈታው አመራሩን በማጠናከር ሰላምና ፀጥታን በማስፈን ነው ብለዋል።
ብልጽግና ችግሮችን ከሕዝቡ ጋር በመወያየት ለችግሮች መፍትሄ ለመስጠት እቅድ በማቀድ እስከ ከታችኛው ቀበሌ መዋቅር ድረስ ማኅበረሰቡን በማወያየት ይሰራል ሲሉም ገልጸዋል።
ምንይሉ ደስይበለው (ከባሕር ዳር)