ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ባህል የሕዝቦች የኪነ-ጥበብና ስልጣኔ ምልክት መሆኑን ገለጹ

ነሐሴ 12/2014 (ዋልታ) ባህል የአንድ አካባቢ ሕዝቦች የአብሮነታቸው ማሳያና የማንነታቸው መገለጫ ከመሆኑም ባሻገር የለውጥና እድገት፤ የኪነጥበብና ስልጣኔ ምልክት ጭምር መሆኑን የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች አሸንድዬ፣ ሻደይና ሶለል በዓል በልዩ ልዩ ባህላዊ ክዋኔዎች ይከበራሉ።

ርዕሰ መስተዳድሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት በዓላቱን ስናከብር መረዳዳትና መደጋገፍን በተግባር የምናሳይበት ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡

በዓላቱ ወጣቶችና ልጃገረዶች አደባባይ ወጥተው፣ በአንድነት ተሰባስበው ባህልና እሴቶቻቸውን በመግለጽ የሚያሳልፉበትና በመካከላቸው ጠንካራ የባህል ትስስር የሚፈጥሩበት ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ እነዚህ የአደባባይ በዓላት በሕዝቦች መካከል ማኅበራዊ ትስስር በመፍጠር አንድነትን ያጠናክራሉ፤ ያጸናሉ ብለዋል።

በአንድነት ውስጥ መተዋወቅና መከባባርን፤ በመከባባር ውስጥ ደግሞ የጋራ ሰላምና ልማትን እንደሚገነቡ አስረድተዋል፡፡

በመሆኑም በዓላቱን ወቅት ጠብቀን ከማክበር ባለፈ በቅርስነት ጠብቀን፣ ለክልላችን ቱሪዝም ልማት እድገት የድርሻውን እንዲያበረክቱ በአግባቡና በተገቢው መንገድ በማስተዋወቅ ልንጠቀምባቸው የሚገቡ እሴቶቻችን መሆናቸውን ገልጸዋል።