ሚያዝያ 14/2014 (ዋልታ) የአማራ ክልል እና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድሮቹ ለትንሳኤ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ፡፡
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ሞትን አሸንፎ ከመነሣት፣ ከመቃብርና ጨለማ ከመውጣት፣ ከሲኦልና እስራት ከመፈታት የሚበልጥ ምንም ደስታ ሊኖር አይችልም፤ ትንሳኤም በአዳም ላይ የተፈረደው ፍርድ ሁሉ ተደምስሶ፣ ፍጹም ነፃነት፣ የማይለወጥ ደስታ የተገኝበት ነው ብለዋል፡፡
የክልሉ መንግሥት በጦርነት እና በተለያዩ ግጭቶች ምክንያት ተፈናቅለው በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ወገኖቻች በዓሉን በአብሮነትና በደስታ እንዲያሳልፉ አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ላይ ይገኛል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ የወገኖቻችን ችግሮ ከመጋራት በላይ ደስታ ስለማይኖር በቀጣይም የተፈናቀሉ ወገኖችን በዘላቂነት ለማቋቋም የምናደርገው ጥረት አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።
ኅብረተሰቡ የትንሣኤ በዓልን ሲያከብር ወገኖችን በመደገፍና ማዕድ በማጋራት ወገናዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) በቡኩላቸው የስቅለት እና የትንሳኤ በዓልን በማስመልከት ለክርስትና እምነት ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በመልዕክታቸው በዓሉ ስለሰው ልጆች ፍቅር በመስቀል ላይ በተከፈለ ዋጋ የተገኘ መሆኑን አስታውሰው ያለንን ማኅበራዊ አንድነታችንን በማጠናከር፣ በመዋደድና በመከባበር ማክበር ከሁላችንም ይጠበቃል ብለዋል።
ለአረጋዊያንና አቅመ ደካሞች ፍቅርና ክብር በማሳየት በዓሉን እንደ አንድ ቤተሰብ ማክበር እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡
ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW
ቴሌግራም https://t.me/WALTATVEth
ዩቲዩብ https://www.youtube.com/c/WaltaTV/featured
ቲዊተር https://twitter.com/walta_info
አብራችሁን ስለሆናችሁ እናመሰግናለን!