ርዕሰ መስተዳድሮቹ ሸኔን ጨምሮ ህገ-ወጥ ኃይሎች ላይ የሚወሰደው ህግ የማስከበር እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለጹ

ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ

ሰኔ 15/2014 (ዋልታ) አሸባሪው ሸኔን ጨምሮ በሌሎች ህገ-ወጥ ኃይሎች ላይ የሚወሰደው ህግ የማስከበር እርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ የኦሮሚያና አማራ ክልሎች ርዕሰ መስተዳድሮች ገለጹ፡፡

የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ መደበኛ ስብሰባውን እያካሄደ ሲሆን ኮሚቴው በስብሰባው በወቅታዊ ሀገራዊ የጸጥታ ጉዳይ እና እየተወሰደ ባለው የሕግ ማስከበር እርምጃ ላይ ተወያይቷል።

የኦሮሚያና አማራ ክልሎች ርዕሰ መስተዳድሮችና የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ሽመልስ አብዲሳ እና ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) የሽብር ቡድኑ በንጹሃን ዜጎች ላይ ያደረሰው ጥቃት የሁሉም ኢትዮጵያውያን ጠላት መሆኑን ያረጋገጠ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው የሽብር ቡድኑ ከሰሞኑ በኦሮሚያ ክልል በሚኖሩ ሰላማዊ ዜጎች ላይ ያደረሰውን ጥቃት አውግዘው በቡድኑ ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አቅጣጫ መቀመጡን አውስተዋል።

አሁን ላይ የጸጥታ ኃይሉ ከሕዝብ ጋር በመቀናጀት በሽብር ቡድኑ ላይ እየወሰደ ባለው እርምጃ እጅግ አበረታች ውጤት እየተመዘገበ መሆኑንም አንስተዋል።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድርና የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) በበኩላቸው የብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ለሕዝብ ጥያቄ ምላሽ የሰጡ ህግ የማስከበር እርምጃ መወሰዳቸውን ገልጸዋል፡፡

በዚህም አሸባሪው ሸኔን ጨምሮ የኅብረተሰቡን ሰላምና ደኅንነት አደጋ ላይ ጥለው በነበሩ በርካታ ህገ-ወጥ ኃይሎች ላይ ህግ የማስከበር እርምጃ ተወስዷል ነው ያሉት፡፡

ነገር ግን አሸባሪው ሸኔ ከሰሞኑ የጸጥታ ኃይሎች በሌሉባቸው አካባቢዎች በመሽሎክሎክ በሰላማዊ ዜጎች ላይ ያነጣጠረ አሰቃቂ ጥቃት መፈጸሙን ጠቅሰዋል።

ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር)

የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በዜጎች ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ማውገዙን ጠቅሰው ኮሚቴው በቀጣይም ህግ የማስከበሩ እርምጃ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አቅጣጫ ማስቀመጡን አመላክተዋል።

በየትኛውም ክልል በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚፈጸም ጥቃት የሁሉም ኢትዮጵያውያን ጉዳይ መሆኑን ያብራሩት ርዕሰ መስተዳድሮቹ ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያውያን አንድነታቸውን ጠብቀው የሀገር ጠላት የሆኑ ኃይሎችን በጋራ ሊታገሉ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

አሸባሪው ሸኔ ከሰሞኑን የፈጸመው ጥቃትም ኢትዮጵያውያንን እርስ በርስ ለማባላት ያለመ ሴራ መሆኑንም አመላክተዋል።

በቀጣይም የኢትዮጵያን ሰላምና ደኅንነት ለማረጋገጥ የተጀመረው ህግ የማስከበር ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ማረጋገጣቸውን ኤፍቢሲ ዘግቧል፡፡

ከዚህ አኳያ ኅብረተሰቡ መንግሥት እየወሰደ ላለው ህግ የማስከበር እርምጃ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW