ርዕሰ መስተዳድሮች ሕዝበ ሙስሊሙ የኢድ አልፈጥር በዓልን ሲያከብር በመደጋገፍ ሊሆን ይገባል አሉ

ሚያዝያ 23/2014 (ዋልታ) ሕዝበ ሙስሊሙ የኢድ አልፈጥር በዓልን ሲያከብር አብሮነትንና መደጋገፍን በሚያጠናክር መልኩ ሊሆን እንደሚገባ የክልል ርዕሰ መስተዳድሮች አሳሰቡ፡፡

ርዕሰ መስተዳድሮቹ ለ1ሺሕ 443ኛው ኢድ- አልፈጥር በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ባስተላለፉት መልዕክት የኢድ አልፈጥር  በዓል የመረዳዳት፣ የመተሳሰብና የአብሮነት በዓል ነው ብለዋል፡፡

በቀጣዩም ጊዜ ይህንኑ መረዳዳትና አብሮነት በማጠናከር ሰላማችንን ዘላቂ የምናደርግበት ሊሆን ይገባል ነው ያሉት፡፡

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) በበኩላቸው የሀገሪቱ ሕዝብ ለዘመናት የተገመደበት የአብሮነት ገመድ በዚህ በዓል ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል፡፡

በዓሉን ስናከብርም የአብሮነትና የሰላም እሴቶቻንን ከሚያጎድፉ ተግባራት በመታቀብ የኢትዮጵያን ከፍታ እውን ለማድረግ በሚደረገው ጥረት የበኩላችንን ሚና በመወጣት መሆን እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኡሞድ ኡጁሉ ሕዝበ ሙስሊሙ የኢድ አል ፈጥር በዓልን ሲያከብር ፍቅርን፣ መተሳሰብንና አንድነትን በማጠናከር ሊሆን እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡

ሕዝቡ በጾም ወራት ያሳየውን መተሳሰብ በበዓሉ ወቅትም ሆነ በሌሎቹ ጊዜያት መድገም አለበት ያሉት ርዕሰ መስተዳደሩ እየተፈጠረ ያለውን አለመግባባት ለመቅረፍ እንዲሁም የመከባበርና የመቻቻል እሴት ቀድሞ ወደነበረበት ሁኔታ ለመመለስ ሁሉም የበኩሉን ኃላፊነት ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል።