ሰላማዊ ትግልን የተቀላቀለው የአሸባሪው ሸኔ አዛዥ

መስከረም 10/2014 (ዋልታ) የ ሸኔ የደቡብ ኦሮሚያ ዞን አዛዥ ጎልቻ ዴንጌ የቀረበውን የሰላም ጥሪ ተቀበሎ ወደ አገር ቤት ተመለሰ፡፡

ጎልቻ ዴንጌ ከኬንያ ናይሮቢ ተነስቶ ቦሌ ዓለም ዐቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ የኦሮሚያ ክልል የመንግሥት ባለሥልጣናት አቀባበል አድርገውለታል፡፡

አሸባሪው ሕወሓት እና ሸኔ ጥምረት በመፍጠር ኢትዮጵያን እናፈርሳለን በማለት እየሄዱበት ያለውን ሴራ አልቀበልም በማለት  የሰላም መንገድን መምረጡን አስታውቋል፡፡

አሁንም በጫካ የሚገኙ የአሸባሪው ሸኔ ታጣቂዎች የኦሮሞ ሕዝብን ከፍተኛ ዋጋ እያስከፈለ የሚገኘውን ውጤት አልባ ትግል አቁመው የሱን ፈለግ በመከተል ሰላማዊ መንገድን እንዲመርጡም ጥሪ አስተላልፏል፡፡

አገር ፈተና ውስጥ በገባችበት በዚህ ወቅት ከኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር ማበር ታሪክ ይቅር የማይለው ክህደት ነው ሲል የኦሮሞ ሕዝብ አንድነቱን በማጠናከር በኢትዮጵያ ላይ የተቃጣውን ወረራ ሊመክት ይገባል ብለዋል፡፡

በአቀባበል ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የኦሮሚያ ክልል መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ጌታቸው ባልቻ የክልሉ መንግሥት ያቀረበውን ጥሪ በመቀበል ጎልቻ ዴንጌ የሰላም መንገድን መምረጡ አገር የማዳን ውሳኔ ነው ብለዋል፡፡ የክልሉ መንግሥት አሁንም ቢሆን በሰላማዊ መንገድ መታገል ለሚፈልጉ ሁሉ በሩ ክፍት ነው ብለዋል፡፡

ጎልቻ ዴንጌ ከ28 ዓመታት በኋላ ከኬንያ ወደ ኢትዮጵያ የተመለሰ ሲሆን በጉጂ እና ቦረና የሚንቀሳቀሰውን የሸኔ ክንፍ ታጣቂዎችን ሲመራ የነበረ ነው፡፡

በአሳየናቸው ክፍሌ