ሰሞኑን ጀርመን አደባባይ አካባቢ በተከሰተው ከባድ የጎርፍ አደጋ ሕይወታቸውን ላጡ ነዋሪዎች የከተማ አስተዳደሩ ድጋፍ አደረገ

ነሀሴ 14/2013 (ዋልታ) – ሰሞኑን በአዲስ አበባ ጀርመን አደባባይ አካባቢ በሚገኘው የጉዲና አቶምሳ ቤተክርስቲያን ማሰልጠኛ ማእከል ውስጥ በተከሰተው ከባድ የጎርፍ አደጋ ሕይወታቸውን ላጡ 8 ነዋሪዎች የከተማ አስተዳደሩ የተለያዩ ድጋፎችን አድርጓል።
 
ድጋፉን ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ፤በምክትል ከንቲባ ማእረግ የማዘጋጃ ቤታዊ ዘርፍ ስራ አስኪያጅ አቶ ጥራቱ በየነ ጋር በመሆን በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች በጉዲና ቱምሳ የስልጠና ማዕከል በመገኘት አስረክበዋል ።
 
የከተማ አስተዳደሩ ለተጎጂ ቤተሰቦች የሚውል ከ1.3 ሚሊዮን በላይ ብር ድጋፍንም የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን መካነ ኢየሱስ ፕሬዝዳንት ቄስ ዮናስ ይገዙ ከምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ እጅ ተረክበዋል።
 
ድጋፉ ለቤት ኪራይ እና ተጎጂዎችን መልሶ ለማቋቋም ይውላል ተብሏል።
 
ከ216 ሺህ ብር በላይ ወጪ የተገዙ የተለያዩ ቁሳቁስ ድጋፍም ተደርጓል።
 
ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በቀጣይም የከተማ አስተዳደሩ ከተጎጂዎች ጎን እንደሚቆም እና ችግሩን እንደሚካፈል አስታውቀዋል።
 
የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማም ለተጎጂዎች የ100 ሺህ ብር ድጋፍ አበርክቷል።
 
ከአዲስ አበባ ወደ ሆሳእና አስከሬን መሸኘቱን ተከትሎም የከተማ አስተዳደሩ ተወካዮች ስፍራው ድረስ በመጓዝ እንደሚያፅናኑ ወ/ሮ አዳነች ገልፀዋል።
 
የአዲስ አበባ ከተማ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽንም በመዲናዋ የጎርፍ አደጋ በተከሰተባቸው በአጉስታ፣ ወይራ፣ መካኒሳ እና ጎፋ አካባቢዎች ለሚገኙ 650 ለሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ከ1.5 ሚኒሊዮን ብር በላይ የአይነት እና የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል።
 
የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን መካነ ኢየሱስ ፕሬዝዳንት ቄስ ዮናስ ይገዙ በበኩላቸው የከተማ አስተዳደሩ የጎርፍ አደጋው ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮ ለተጎጂዎች የህክምናና ሌሎች ድጋፎችን ለማድረግ ያሳየው ጥረት የሚደነቅ መሆኑን እንደሆነ መግለጻቸውን ከአዲስ አበባ ፕሬስ ሴክሬተሪ ቢሮ ያኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡