ነሐሴ 24/2016 (አዲስ ዋልታ) የምስራቅ ዕዝ ሰራዊት ለሐረሪ ክልል ሰላምና መረጋጋት የከፈለውን መስዋዕትነት የክልሉ ሕዝብ መቼም የማይረሳው ነው ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ገለጹ።
የመከላከያ ሰራዊቱ በተለይ የምስራቅ ዕዝ አባላት ለሐረሪ ክልልና ምስራቁ የኢትዮጵያ ክፍል ሰላምና መረጋጋት እንዲሁም ለሕግ የበላይነት መከበር አስተዋጽኦ ማድረጉን አመልክተዋል።
የምስራቅ ዕዝ እድሜ ጠገብነቱን ያነሱት ርዕሰ መስተዳድሩ የአካባቢውን ደህንነት ለማረጋገጥ በከፈለው መስዋትነት የምስራቁ የአገሪቱ ክፍል መገለጫ መሆን መቻሉን ተናግረዋል።
የምስራቅ ዕዝ የሐረሪ ክልልን ፀጥታ ከማስከበር አኳያ ከፍተኛ ሚና መጫወቱንና አሁንም በምስራቅ የአገሪቷ ክፍል ዘላቂ ሰላም ለማስፈን እየሰራ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
ሰራዊቱ ሰላምና ደህንነትን ከማረጋገጥ ባሻገር በልማት ስራዎች በመሳተፍ የበኩሉን አሻራ እያኖረ ይገኛል ብለዋል።
የክልሉ መንግስት የምስራቅ ዕዝ 47ኛ ዓመት የምስረታ በዓልን እንደ አንድ መልካም አጋጣሚ በመውሰድ ከዕዙ ጋር የነበረውን መልካም ግንኙነት ይበልጥ ለማጎልበት እንደሚሰራ ተናግረዋል።
የምስረታ በዓሉ በተለይ ዕዙና የአገር መከላከያ ሰራዊት በአጠቃላይ አንድነቱን የሚያፀናበት፣ በሰላምና ልማት ዘርፍ የተመዘገቡ ድሎችን ይበልጥ የሚያሰፋበት አዲስ ምዕራፍ መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ መግለጻቸውን ከክልሉ ኮሙዩኒኬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።