ጳጉሜን 2/2016 (አዲስ ዋልታ) ሰራዊቱ ከየትኛውም ወገን የሚቃጡ ጥቃቶችን በአስተማማኝ ደረጃ ለመመከት የሚያስችል ዝግጁነት እንዳለው የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለፁ፡፡
የምስራቅ ዕዝ 47ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ማጠቃለያ መርሃግብር የሰራዊት አዛዦች፣ የመንግስት ከፍተኛ አመራሮችና የሰራዊቱ አባላት በተገኙበት በሐረር ከተማ ተካሂዷል።
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ሰራዊቱ ዛሬም እንደትናንቱ የተሰጠውን ግዳጅ በታላቅ ጀግንነትና ስነምግባር እየተወጣ እንደሚገኝ ገልጸው ሀገራችን ኢትዮጵያ ለሶማሊያ ሰላምና መረጋጋት የራሷን መከላከያ በመላክ ከሁሉም የላቀ ከፍተኛ ድጋፍ ማድረጓን ገልፀዋል፡፡
ዛሬ ላይ የተወሰኑ የሶማሊያ ባለስልጣናት ህይወቱን የገበረላቸው ሰራዊት እንደጠላት መመልኩት አሳዛኝ መሆኑን ተናግረዋል።
የምስራቅ ዕዝ አዛዥ ሌተናል ጀነራል መሀመድ ተሰማ እንዳሉት በዓሉ ዕዙ ያስመዘገባቸውን አኩሪ ገድሎች ለማሰብና ለማስቀጠል ያለመ መሆኑ ገልጸው በቀጣይም ከየትኛውም ወገንተኝነት በፀዳ መልኩ የተጣለበትን ታላቅ ሀላፊነት ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል።
የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ በበኩላቸው ሰራዊቱ ከየትኛውም ወገን የሚቃጣ ጥቃትን በአስተማማኝ መልኩ አሳፍሮ እንደሚመልስ ያላቸውን መተማመን ገልጸዋል።
ከለውጡ ወዲህ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍንና የህግ የበላይነት እንዲከበር ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ከመሆኑም በተጨማሪ ልማትን ለማረጋገጥ በሚከናወኑ ስራዎች ውስጥ የራሱን አስተዋጽኦ እያበረከ ይገኛል ብለዋል።
በተጨማሪም ዕዙ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በመሬት መንሸራተት ምክንያት ለተጎዱ ወገኖች ከምስራቅ ዕዝ የሰራዊት አባላት የተዋጣ አምስት ሚሊየን ብር ድጋፍ መደረጉም ተገልጿል፡፡
”እኛ የምስራቅ ቁጮ የኢትዮጵያ ወታደሮች ነን” በሚል መሪ ቃል በተከበረው የምስረታ በዓል ላይም የሀረሪ ክልል፣ የምስራቅ ሀረርጌ፣ የድሬዳዋ አስተዳደርና የሶማሌ ክልል አመራሮችና ነዋሪዎች ተገኝተዋል።
በተስፋዬ ኃይሉ (ከሀረሪ)