ሰራዊቱ የሀገርን ሉአላዊነትና የዜጎችን ደህንነት ለመጠበቅ ተዘጋጅቷል – ሻለቃ ሽፈራው ሽብሩ

ሐምሌ 16/2013 (ዋልታ) – ሰራዊቱ የሀገርን ሉአላዊነትና የዜጎችን ደህንነት ለመጠበቅ ከምንጊዜውም በላይ መዘጋጀቱን ሻለቃ ሽፈራው ሽብሩ አስታወቁ።

በኢፌዴሪ የመከላከያ ሚኒስቴር የሰላም ማስከበር ማዕከል የሁርሶ ኮንቲንጀንት ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት የ3ኛ ብርጌድ 3ኛ ሻለቃ ምክትል አዛዥ ሻለቃ ሽፈራው ሽብሩ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ሠራዊቱ ከውጭና ከውስጥ የሚቃጡ ትንኮሳዎች ለማምከንና ለመምታት ከምንጊዜውም በላይ በተጠንቀቅ ላይ ይገኛል።

ሰራዊቱ የዜጎችን ደህንነት ከማስከበር ባለፈ የሀገርን ዕድገት ወደ ከፍታ የሚያሸጋግሩ መሰረተ ልማቶችን በተጠንቀቅ እየጠበቀ መሆኑን ተናግረዋል።

“ሠራዊቱ በተለይም የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን እንደ አይኑ ብሌን ከውጭና ከውስጥ ጠላት እየጠበቀ ይገኛል” ሲሉ ለአብነት ጠቅሰዋል።

የህዳሴው ግድብ ምልክት የሆነው ዋንጫ ድሬዳዋ መምጣቱ ሰራዊቱ ድጋፉን እንዲያጠናክር መልካም አጋጣሚ የሚፈጥር መሆኑን ጠቁመው ዋንጫው በድሬዳዋ ቆይታው ከሚዘዋወርባቸው አካባቢዎች አንዱ የሁርሶ ኮንቲንጀንት ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት መሆኑን ጠቁመዋል።

የሁርሶ ኮንቲንጀንት ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት የሚያስመርቃቸው ምልምል የሰራዊት አባላት ህገ መንግስታዊ ስርአቱንና የሀገር ሉአላዊነት የማስከበር ተግባርን ለማጠናከር ወሳኝ ሚና እንደሚጫወቱ ሻለቃ ሽፈራው አመልክተዋል።

ከትምህርት ቤቱ የሚመረቁ ወታደሮች የተጣለባቸውን ሀገራዊ ተልዕኮ በከፍተኛ ወኔ የመፈጸም ብቃት ያላቸው መሆኑንም አስታውቀዋል።