ሰብአዊ ድጋፍ ለማድረግ ለሚንቀሳቀሱ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች የክልሉ መንግስት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር በትብብር ይሰራል – ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ

ሐምሌ 19/2015 (ዋልታ) የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) ሰብአዊ ድጋፍ ለሚሹ ዜጎች ድጋፍ ለማድረግ ለሚንቀሳቀሱ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች የክልሉ መንግስት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር በትብብር እንደሚሰራ ገለጹ፡፡

ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) ከዓለም የምግብ ፕሮግራም ተወካይ ክሪስ ኒኮል ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች ሰብዓዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች በድርጅቱ በኩል የተከናወኑ ተግባራትና በቀጣይ የሚተገበሩ ስራዎችን አንስተዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ የዓለም ምግብ ፕሮግራም በክልሉ እርዳታ ለሚፈልጉ ዜጎች በቀዳሚነት ሰብዓዊ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልጸው ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በቀጣይም ሰብአዊ ድጋፍ ለሚሹ ዜጎች ድጋፍ ለማድረግ ለሚንቀሳቀሱ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች የክልሉ መንግስት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር በትብብር ይሰራል ብለዋል፡፡

አሁንም የዕለት ደራሽ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው በርካታ ዜጎች መኖራቸውን የጠቆሙት ርዕሰ መስተዳድሩ ሌሎች ግብረ ሰናይ ድርጅቶችም ተመሳሳይ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም በኢትዮጵያ ተወካይ እና ካንትሪ ዳይሬክተር ክሪስ ኒኮል በበኩላቸው ድርጅታቸው ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች ሰብአዊ እርዳታ ሲያቀርብ መቆየቱን አስታውሰዋል።

በቀጣይም የዓለም ምግብ ፕሮግራም በክልሉ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች የሚያደርገውን ሰብዓዊ ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል ማለታቸውን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጽሕፈት ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡