ሰብኣዊ ድጋፍ ወደ ትግራይ እንዳይገባ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እንቅፋት አይደለም – አንፊትስ ጌራልድ

አንፊትስ ጌራልድ

መጋቢት 15/2014 (ዋልታ) ሰብኣዊ ድጋፍ ወደ ትግራይ ክልል እንዳይገባ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እንቅፋት እንዳልሆነ በአፍሪካ ቀንድ የደኅንነት እና ፍትህ አማካሪ አንፊትስ ጌራልድ ገለጹ።

ጌራልድ (ፕሮፌሰር) ይህን ያሉት የአሸባሪ ቡድኑ ትሕነግ አባልና የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር ቴድሮስ አድሓኖም በትዊተር ገጻቸው ያሰፈሩትን ውንጀላ ተከትሎ በሰጡት ምላሽ ነው።

ዳይሬክተሩ የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ወታደሮች መንገድ በመዝጋት የሰብኣዊ እርዳታ ወደ ትግራይ እንዳይገባ አግደዋል ሲሉ የተለመደ መሰረተ-ቢስ ውንጀላ መሰንዘራቸው ይታወሳል።

አማካሪዋ ይህን የቴድሮስ አድሓኖምን ውንጀላ ተከትሎ ባሰፈሩት ሃሳብ ሰብኣዊ ድጋፉ በሚተላለፍበት የአፋር ክልል ውስጥ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አለመኖሩን እስካሁን ያሉ መረጃዎች ማረጋገጣቸውን ጠቁመዋል።

በተቃራኒው የትሕነግ ታጣቂዎች በአፋር ክልል በሚገኙ አምስት አካባቢዎች መስፈራቸውን ገልጸው እውነታው ይህ ከሆነ ከአፋር ወደ ትግራይ የሚወስደው መንገድ በምን ምክንያት ሊዘጋ ቻለ? ሲሉም ይጠይቃሉ።

በመሆኑም እዚያ አካባቢ ያለውን ሁኔታ በግልጽ ለመረዳት ያላሰለሰ ጥረት እና ጥናት ያስፈልጋል ሲሉ የቴድሮስን ውንጀላ መረጃ አልባ መሆኑን በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት አመላክተዋል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW