ሰብዓዊ ድጋፍን ከህዝብ ጎሮሮ የሚነጥቀው ትህነግ
በሱራፌል መንግሥቴ
ነሐሴ 30/2014 (ዋልታ) አሸባሪው የትህነግ ቡድን የትግራይ ሴቶች እና ህፃናትን ያለምንም ወታደራዊ ስልጠና ወደ ጦርነት በመማገድ የግል ፍላጎቱ መጠቀሚያ እና የስልጣን እድሜ ማራዘሚያ እያደረጋቸው ይገኛል።
የሽብር ቡድኑ እድሜያቸው ለውትድርና አገልግሎት ያልደረሱና ብቁ ያልሆኑ ህፃናት እና ሴቶችን በተሳሳተ የሀሰት ፕሮፓጋንዳ በማስገደድ ለእንግልት ብሎም ጦርነት ላይ እንዲሳተፉ በማድረግ ሰላም ፈላጊ አለመሆኑን በተደጋጋሚ በማሳየት ላይ ነው።
የሽብር ቡድኑ ስልጣን ላይ በነበረበት ወቅትም ቢሆን ለትግራይ ህዝብ የፈየደው ነገር ካለመኖሩ ባሻገር ህዝቡን በአፈና ውስጥ በማቆየት የፖለቲካ ጥቅሙ መነገጃ ሲያደርገው ቆይቷል።
የትህነግ ቡድን ከምስረታው ጀምሮ ህዝብን በመነጣጠል የራሱን ዓላማ ለማሳካት የሚሯሯጥ የጥፋት ስብስብ መሆኑንም በተግባር ያሳየ ነው።
ቡድኑ አሁንም ቢሆን ወደ ሰላም እንዲመጣና በአፈና ውስጥ ያለው የትግራይ ህዝብ ሰቆቃ እንዲቆም ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ በመንግስት በኩል ቢደረግለትም ሰላም አያስፈልገኝም አሻፈረኝ በማለት ሦስተኛ ዙር ጦርነት ከፍቶ በርካታ የትግራይ ወጣቶችን እያስፈጀ ይገኛል፡፡
ትህነግ በከፈተው ጦርነት የተነሳም እድሜያቸው ለጦርነት ያልደረሰ ህፃናትና ሴቶችን በጦር ግንባር በማሰለፍ ለትግራይ ህዝብም ደንታ እንደሌለው ጭምር አሳይቷል።
አሸባሪው ትህነግ ጦርነት የከፈተበት ምክንያት የማሸነፍ ዓላማ ይዞ ሳይሆን ሰላም ሲሆን ከትግራይ ሕዝብ የሚነሳውን ጥያቄ ለመደበቅና ሕዝቡ እንደሚያጠፋው ስለተገነዘበ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡
ሰብዓዊነትን ፈፅሞ የማያውቀው ትህነግ በጦርነት ወቅት ለትግራይ ህዝብ ሰብዓዊ ድጋፍ ተብሎ ከዓለም አቀፍ የረድኤት ድርጅቶች ወደ ትግራይ ክልል ይገባ የነበረውን እርዳታም ለወታደራዊ ዓላማ በመጠቀም የትግራይ ህዝብ ላይ ከፍተኛ በደል ፈፅሟል።
ቡድኑ በሰብዓዊነት ሰበብ የመነገድ ልምዱ አሁን የጀመረ አይደለም፤ ከትጥቅ ትግል ጀምሮ ሰብዓዊ ድጋፍን ለጦርነት በማዋልም ይታወቃል።
በ1977 ዓ.ም በትግራይ የተከሰተውን ረሃብ እንደ ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ለትግራይ ህዝብ የሚቀርበውን ድጋፍ ለጦር መሳሪያ መግዣ በማዋል በርካታ የትግራይ ህዝብ በረሃብ እንዲሞቱ አድርጓል፡፡
ይህ ብቻ አይደለም በጦርነቱ ወቅት የሰብዓዊ እርዳታ ጭነው ወደ ክልሉ የገቡ ተሽከርካሪዎችን ለወታደራዊ ዓላማ ሲጠቀምባቸው እንደቆየም የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው።
ትህነግ ዳግም የከፈተውን ጦርነት ከጥምር ኃይሉ ጋር እየተከላከለ የሚገኘው መንግስት የቡድኑ እኩይ ዓላማ እንዳይሳካ በማድረግ የአገሪቱን ልዑላዊነት የማስከበር ግዴታ እየተወጣ ይገኛል።
ታዲያ ይህ የሽብር ቡድን ለትግራይ ህዝብ ተብለው የመጡ ሰብዓዊ እርዳታዎችን ከትግራይ ህዝብ ጉሮሮ ላይ በመንጠቅ ለወታደራዊ ዓላማው ማዋሉን ቀጥሏል።
በሚያሰራጫቸው የሀሰት ፕሮፓጋንዳዎች ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የተሳሳተ ትርክት የሚያስተጋባው ትህነግ በተለይም ህፃናት፣ ሴቶችና አረጋዊያን በረሀብ እያለቁ ነው በሚል የሚያገኘውን ሰብዓዊ ድጋፍ ለወታደራዊ ዓላማ ይጠቀምበታል።
መንግስት ለትግራይ ህዝብ ሰላምና ደኅንነት ሲል የተናጥል የተኩስ አቁም በማወጅ በርካታ ሰብዓዊ ድጋፎች ወደ ትግራይ ክልል እንዲገባ ማድረጉ ይታወሳል።
ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት በተደጋጋሚ ሲያሳይ የቆየው መንግስት አሁንም ድረስ ጦርነት መፍትሄ እንዳልሆነና የሽብር ቡድኑ ወደ ሰላም እንዲመጣ በርካታ ጥረቶችን አድርጓል፤ እያደረገም ይገኛል።
ይሁን እንጂ ትህነግ መንግስት ያቀረበውን የሰላም አማራጭ ወደጎን በመተው ህፃናትና ሴቶችን ሂውማን ዌቭ ወይም የሰው ማዕበል የጦርነት ስልትን በመጠቀም በአንድ ጎን ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የትግራይ ህፃናትና ሴቶች ለረሀብ ተጋልጠዋል እያለ በሌላ በኩል ደግሞ ወደ ጦርነት እያስገባቸው እንደሚገኝ መመልከት ተችሏል።
ቡድኑ ይህን ተግባር ሲፈፅም ለትግራይ ህፃናትም ሆነ ሴቶችና አረጋዊያን ደንታ የሌለው መሆኑን የሚያሳይ እንደሆነም ነው በተደጋጋሚ የሚነገረው።
አሜሪካና አንዳንድ ምዕራባዊያን አገራት ትህነግ የሚፈፅማቸውን ኢሰብዓዊ ድርጊቶች ችላ በማለት ወገንተኝነታቸውን በማሳየት ላይ ናቸው።
በተለይም እንደ ቢቢሲና አልጀዚራ ያሉ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን የቡድኑን የሀሰት ትርክት በማስተጋባት የተዛባ መረጃ በማሰራጨት ላይ ይገኛሉ።
ሰብዓዊ ድጋፍን ለወታደራዊ ዓላማ ተጠቅሞ በትግራይ ህዝብ ስም የሚነግደውን ትህነግ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ማጋለጥ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ሚና መሆን ይኖርበታል።
በተለይም የሽብር ቡድኑን እኩይ ሴራ እያዩ እንዳላዩ የሚያልፉ አንዳንድ ምዕራባዊያን አገራትና ዓለም አቀፍ ተቋማት ቡድኑ በንፁሀን ዜጎች ላይ የሚፈፅማቸውን ከሰብዓዊነት የወጣ ተግባር በማስረጃ አስደግፎ ማሳየት ለነገ የማይባል ተግባር ነው።
በታሪክም ቢሆን አገር ሊያፈርስ በመጣ ጠላት ድርድር የማያውቁት ኢትዮጵያዊያን ከአገር መከላከያ ሰራዊት ጎን መቆም የሚያስፈልግ ጊዜ ላይ ነው።
ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW
ቴሌግራም https://t.me/WALTATVEth
ዩቲዩብ https://www.youtube.com/c/WaltaTV/featured
ቲዊተር https://twitter.com/walta_info
አብራችሁን ስለሆናችሁ እናመሰግናለን!