ሱዳን ወታደሮቼ በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ተገድለዋል በማለት የሀሰት መረጃ እያሰራጨች ነው

ሰኔ 21/2014 (ዋልታ) አንዳንድ የሱዳን መገናኛ ብዙኃን በተለይም ደግሞ እንደ ሱና ያሉ በአገሪቱ መንግሥት የሚደገፉ መገናኛ ብዙኃን አንድ ሲቪልን ጨምሮ ሰባት ወታደሮች በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ተገድለዋል በማለት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ባልፈጸመው ድርጊት የሀሰት ዘገባ እያሰራጩ ይገኛሉ፡፡

የሱዳን መከላከያም ከሁለት ቀናት በፊት ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያ ወታደሮች ወደ ኢትዮጵያ ሰርገው የገቡ ምርኮኛ ሱዳናዊያንን ከገደሉ በኋላ “አስከሬናቸውን ለሕዝብ በአደባባይ አሳይተዋል” ሲል መሰረተ ቢስ ክስ በማቅረብ ለድርጊቱ “ምላሽ እሰጣለሁ” ማለቱ አስገራሚ ሆኗል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በምላሹ የሱዳን መከላከያ በድንበር አካባቢ ያለውን ውጥረት ምክንያት በማድረግ እያደረገ ካለው ትንኮሳ እንዲቆጠብ ጠይቋል፡፡ ድርጊቱ ሆን ተብሎ በሱዳን በኩል የተፈጸመ ጠብ ጫሪነት ያስከተለው ጉዳት መሆኑን በመግለጽም ውጥረቱ ረግቦ አለመግባባቶች መፍትሔ እንዲበጅላቸው ጥሪ አቅርቧል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ድርጊቱ በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ የተፈጸመው ከአሸባሪው ሕወሓት አባላት ጋር ትስስር ያለው የሱዳን መደበኛ ሰራዊት የኢትዮጵያን መሬት ከወረረ በኋላ መሆኑን አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያን ድንበር ጥሶ በመግባት ፀብ ጫሪ ድርጊት የፈፀመው የሱዳን ጦር ሆኖ ሳለ በሁኔታው ኢትዮጵያን ተጠያቂ ለማድረግ የሚሞከርን የትኛውንም ድርጊት እንደማይቀበል የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አፅንኦት ሰጥቷል፡፡

በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ ምርመራ አካሂዳለው ያለው የኢትዮጵያ መንግሥት የሱዳን መንግሥት ሁኔታዎችን ከማባባስ እንዲቆጠብ ጠይቆ ኢትዮጵያ ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ቁርጠኛ መሆኗንም አረጋግጧል፡፡

የሱዳን መንግሥት ሉዓላዊ የሆነውን የኢትዮጵያ ድንበር ጥሶ በመግባት ግልጽ ወረራ ፈጽሞ እያለ ችግሩን አሁንም በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የኢትዮጵያ መንግሥት ቁርጠኛ አቋም እንዳለውም ማስታወቁ ይታወሳል፡፡

ነገር ግን የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት በጥብቅ ሥነ ምግባር የሚመራ እንጂ እንደሽፍታ ገብቶ ጥቃት የሚፈጽም እንዳልሆነ ሊታወቅ ይገባል ሲልም አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊትም ሱዳን በ3ኛ ወገን ተገፋፍታ መጠቀሚያ ከመሆን ይልቅ የሁለቱን ሀገራት ታሪካዊ ግንኙነት በማስታወስ ከፀብ አጫሪ ድርጊቷ እንድትቆጠብ አሳስቧል፡፡

የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት በሱዳን መከላለከያ ሰራዊት አባላት ላይ ምንም አይነት እርምጃ አለመውሰዱን እና ከሥነ ምግባር ውጪ የሆነ ድርጊት እንዳልፈፀመ ገልጿል፡፡

የሱዳን ሰራዊት ወረራ በፈፀመበት የኢትዮጵያ ግዛት ከአካባቢው ሚሊሻዎች ጋር የተፈጠረ ግጭት መኖሩን በመግለፅም በሁለቱም በኩል ተጎጂዎች መኖራቸውን አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ከዚህ ቀደምም በተደጋጋሚ ሲገልጸው እንደቆየው በሁለቱ አገራት ድንበር በተለይም በአልፋሻጋ አካባቢ ያለውን ጉዳይ በወዳጅነት ለመፍታት ሰላማዊ የውይይት መንገድ እንደሚመርጥ መግለፁ አይዘነጋም፡፡

ሱዳን ትሪቡን የተሰኘው የገጸ ድር ዜና ምንጭ ባሳለፍነው ሳምንት ወታደራዊ ምንጮችን አናግሬ ሰራሁት ባለው ዘገባ የሱዳን ወታደሮች በሁለቱ አገራት ድንበር አካባቢ በምትገኘው አል ቁራሺ ከተማ ላይ እርምጃ ከወሰዱ በኋላ ግጭት መቀስቀሱን አስነብቧል።

የሁለቱን አገራት አለመግባባት ለመቅረፍ ኢትዮጵያ ጉዳዩ በድርድር ይፈታ ዘንድ ሱዳን በወረራ የያዘችውን መሬት መልቀቅ አለባት የሚል ቅድመ ሁኔታ አስቀምጣለች።

ሱዳን የውስጥ ችግሮችን ውጫዊ ለማድረግ ስትል በኢትዮጵያ የተፈጠረውን አለመረጋጋት እንደ ዕድል በመጠቀም የኢትዮጵያን ድንበር ጥሳ ገብታለች፡፡ ሱዳን በማን አለብኝነት ስሜት በአካባቢው መሰረተ ልማቶችን ለመገንባትም ጥረት እያደረገች እንደሚገኝ ሲዘገብ ቆይቷል፡፡

ጦሩ መሰረተ ልማቶች መገንባቱን አቁሞ ቀድሞ ወደ ነበረበት እንዲመለስ ደጋግማ የጠየቀችው ኢትዮጵያ ሀገራቱን የሚያወዛግቡ የድንበር ጉዳዮች በሁለቱ አገራት የጋራ ኮሚቴ እንዲታይ ጥያቄ አቅርባም ነበር፡፡

ነገር ግን የሱዳን ወታደራዊ መንግሥት የበላይነቱን ለማስቀጠል ሲል በግብፅ ድጋፍ አሸባሪው ሕወሓትና ሌሎች የሽብር ቡድኖችን ጭምር በማገዝ ኢትዮጵያን ለማዳከምና የውስጥ አለመረጋጋቱን እንደ ዕድል ለመጠቀም፣ የታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ 3ኛ ዙር ሙሌትና 2ኛ ተርባይን ሥራ ማስጀመሪያ ሂደትን ለማስተጓጎል፣ በአጠቃላይ የአገሪቱን ሁለንተናዊ ጉዞ ለማሰናከል እንቅስቃሴዎችን ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡

ሱዳን በኢትዮጵያ ጦር ወታደሮቼ ተገደሉብኝ ስትል ያቀረበችውን መሰረተ ቢስ ውንጀላ ተከትሎ አስተያየት ለመስጠት የግብፁን መሪ የቀደማቸው የለም ነበር፡፡

ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ ኤልሲሲ “በወታደሮቹ ሞት እጅጉን አዝኛለሁ” ሲሉ የሀዘን መልዕክት አስተላልፈዋል።

ለዘመናት የቆየውን የኢትዮጵያና ሱዳን ሕዝብ አብሮ የመኖር እሴት ለመሸርሸር ጥሩ አጋጣሚ ያገኙ መሰላቸው ፕሬዝዳንቱ ልባዊ ሀዘን እንደተሰማቸው ለሌተናል ጀነራል አብዱልፈታህ አል ቡርሃን እና ለሱዳን ሕዝብ መግለፃቸውን የአገራቸው የዜና አውታር ዴይሊ ኒውስ ኢጅብት ዘግቧል።

የሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ሊቀመንበር ሌተናል ጀነራል አብዱል ፈታህ አል ቡርሃን በሁለቱ አገራት ድንበር አቅራቢያ ትንሹ ፋሻጋ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚገኙት አል ዑስራ እና ዋድ ኮሊ አካባቢዎች የሚገኘውን የሱዳን ጦር ሰኞ ዕለት ጎብኝተዋል፡፡

ይሁን እንጅ የኢትዮጵያ ሀገር መከላከያ ሰራዊት የኢትዮጵያን ዳር ድንበር እና ሉዓላዊነት የማስከበር ሁለንተናዊ ብቃት እና ቁመና ያለው በጥብቅ ሥነ ምግባር የሚመራ እንዲሁም በተለያ ሀገራት የሰላም ማስከበር ተልዕኮውን በብቃት የተወጣ ሰራዊት መሆኑ የተመሰከረለት ነው፡፡

በሳሙኤል ሓጎስ