ሲሚንቶ ከዛሬ ጀምሮ በነፃ ገበያ ስርዓት እንዲገበያይ ተወሰነ

ሲሚንቶ ገበያ

ሐምሌ 07/2013 (ዋልታ) – የሲሚንቶ ግብይትን የሚወስነው እና በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ተግባራዊ ሲሆን የቆየው መመሪያ መሻሩ ተገለጸ።

በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የንግድና እቃዎች ጥናትና ቁጥጥር ዳይሬክተር አቶ ካሳሁን ሙላት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ከዛሬ ጀምሮ ላልተወሰ ጊዜ ሲሚንቶ በነፃ ገበያ ስርዓት እንዲገበያይ ተወስኗል ብለዋል።

ለዚህም ዋና ምክንያት ክረምት በመሆኑ የግንባታ ስራዎች ስለሚቀንስና ከሱ ጋር ተያይዞ የሲሚንቶ ምርት ፍላጎት ስለሚቅንስ እንዲሁም ከፋብሪካዎች ጋር ችግሩን ለመፍታት ስምምነት ላይ በመደረሱ መሆኑን ተናግረዋል።

በተጨማሪም የሲሚንቶ ምርት እጥረት እንዳይኖር መንግስት ከውጪ ለማስገባት ዝግጅት ማጠናቀቁና ፋብሪካዎች ምርታቸው እንዲጨምር በመደረጉ መሆኑን አቶ ካሳሁን ማብራራታቸውን ኢብኮ ዘግቧል፡፡