“ሲኤንኤን” ኢትዮጵያን በተመለከተ ሃሰተኛ መረጃ እያወጣ እንደሆነ ተጋለጠ

ጥቅምት 27/2014 (ዋልታ) “ሲኤንኤን” የተባለው የቴሌቪዥን ጣቢያ ኢትዮጵያን በተመለከተ ሃሰተኛ መረጃ እያወጣ እንደሆነ ተጋለጠ።

ጣቢያው ኢትዮጵያን በተመለከተ ተደጋጋሚ ዘገባዎችን እየሰራ ቢገኝም፤ የሚሰራቸው ዘገባዎች በትክክለኛ መረጃ ላይ ያልተመሰረቱ ሐሰተኛ፣ የተዛቡና ሚዛናዊነት የጎደላቸው እንደሆኑ ተጠቁሟል።

የቴክኖሎጂ አማካሪና ስትራተጂስት የሆነው የቴክቶክ ዋና አዘጋጅ ሰሎሞን ካሳ በማህበራዊ ትስስር ገጹ ይፋ እንዳደረገው ሲኤንኤን በኢትዮጵያ ስላለው ግጭት በሰራው አንድ ዘገባ ላይ ሀሰተኛ ምስል መጠቀሙን አጋልጧል።

‘ምንም ነገር ተሸሽጎ ለዘላለም አይቆይም’ በሚለው መርሁ የሚታወቀው ኡጋንዳዊው የምርመራ ጋዜጠኛው ዳኒኤል ሉታያ ወደ ኢትዮጵያ ከማቅናቱ በፊት የሲኤንኤን ዘገባዎች ተመልክቶ እንደነበር ገልጾ፤ በዘገባው መሰረት ወደለየለት የጦር ቀጣና እየገባ መሆኑ ተሰምቶት እንደነበር በቲዊተር ገጹ መፃፉን ትላንት መዘገባችን ይታወቃል።

ነገር ግን ኢትዮጵያ ሲደርስ ያጋጠመው የሲኤንኤን ዘገባ ከፈጠረበት ምስል ተቃራኒ እንደሆነ በጽሑፉ ገልጿል።