ሳምንቱ ስኬታማ የዲፕሎማሲ ስራዎች የተከናወኑበት መሆኑ ተገለፀ

ታኅሣሥ 14/2014 (ዋልታ) ሳምንቱ ስኬታማ የዲፕሎማሲ ስራዎች የተከናወኑበት መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
‹‹በተባበሩት መንግሥታት ኢትዮጵያ ላይ የተጠራው ስብሰባ አድሎአዊና የፖለቲካ ዓላማ ያለው መሆኑን ለአፍሪካ አገራት በማስረዳት ከጎናችን እንዲሰለፉ ማድረግ ተችሏል›› ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ገልፀዋል።
በሰብኣዊ መብቶች ምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ ድምፀ ተአቅቦ ላደርጉ የአፍሪካ አገራትም፤ ጉዳዩ መላው አፍሪካን የሚመለከት በመሆኑ ይህንን ማድረግ እንዳልነበረባቸው እያስረዳናቸው ነው ብልዋል።
ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) እንዲሁም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከሰሞኑ ከተለያዩ አገራት መሪዎች ጋር ያደረጉት ውይይት የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ ከማስረዳት አንፃር ውጤታማ እንደነበርም አንስተዋል።
አገራቱ ለኢትዮጵያ የማያወላዳ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ማረጋገጣቸውንና ስኬታማ የሁለትዮሽ ውይይቶች መደረጋቸውንም አንስተዋል።
አሸባሪው ሕወሓት ትምህርት ቤቶች፣ የጤና ተቋማት፣ ሆቴሎችና የተለያዩ ተቋማት ላይ ውድመት ሲያደርስ የዓለም ጤና ድርጅትና ዩኔስኮ ምንም ድምፅ አለማሰማታቸውን አምባሳደሩ ተችተዋል።
የሁለቱ ተቋማት ዝምታ ተገቢ ካለመሆኑም በላይ አሳዛኝ እንደሆነ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል እንደተነገራቸውም አምባሳደር ዲና ገልፀዋል።
በትዕግስት ዘላለም