ሳፋሪ ኮም አገልግሎት መጀመር የሚያስችለውን ኔትዎርክ መገንባቱን አስታወቀ

የካቲት 15/2014 (ዋልታ) ሳፋሪ ኮም የቴሌኮም አገልግሎት መጀመር የሚያስችለውን ኔትዎርክ መገንባቱን አስታወቀ።

በአዲስ አበባ የተገነባው የሳፋሪ ኮም የመጀመሪያው የመረጃ ማዕከል (ዳታ ሴንተር) የድምፅ፣ የፅሑፍ እና የኢንተርኔት ዳታ መስጠት የሚያስችል እንደሆነ የቴክኖሎጂ ኃላፊው ፔድሮ ራባሴል ተናግረዋል።

ኃላፊው በአዲስ አበባ የተገነባውን የመረጃ ማዕከል ለሀገር ውስጥ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች አስጎብኝተዋል።

የመረጃ ማዕከሉ ሙከራውን በተሳካ መንገድ እንዳከናወነም ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ 2ኛው የቴሌኮም አቅራቢ የሚሆነው ሳፋሪ ኮም ለመረጃ መዕከሉ 300 ሚሊየን ዶላር ወጭ አድርጊያለሁ ብሏል።

የቴሌኮም አገልግሎቱን ሚያዝያ  ላይ እንደሚጀምር ያስታወቀው ሳፋሪ ኮም በሚቀጥለው ዓመት 25 በመቶ የኢትዮጵያ ሕዝብን ተደራሽ ለማድረግ እየሰራሁ ነው ሲልም ገልጿል።

ድርጅቱ በ10 ዓመት ውስጥ 8 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር መዋለ ንዋይ ለማፍሰስ እንዳቀደም ነው ያስታወቀው።

በምንይሉ ደስይበለው