በአገር አቀፍ ደረጃ ሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስትራቴጂያካዊና ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ሰፋፊ የንቅናቄ ስራዎች እንደሚካሄዱ የሴቶች፣ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስትር ወይዘሮ ፊልሰን አብዱላሂ ገለጹ።
የኢፌዴሪ የሴቶች፣ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር በስድስት ወራት እቅድ አፈጻጸሙ ዙሪያ በቢሾፍቱ ተወያይቷል።
በውይይቱ ትኩረት በሚሹ ዋና ዋና ነጥቦች ላይ የማጠቃለያ ሀሳብና ቀጣይ አቅጣጫዎችን የሴቶች፣ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስትር ወይዘሮ ፊልሰን አብዱላሂ አስቀምጠዋል።
ባለፉት 6 ወራት የሴቶችንና የወጣቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ብሎም የህጻናትን መብትና ደህንነት ለማጠበቅ የሚያስችሉ በርካታ ውጤታማ ተግባራትን በቅንጅት ማከናወን ተችሏል ብለዋል።
በክልሎችም በመልካም ተሞክሮነት ሊወሰዱና በሌሎችም አካባቢዎች ሊስፋፉ የሚገቡ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውንም በማሳያነት አንስተዋል።
ይሁንና ሴክተሩን አስመልክተው በ10 ዓመቱ የልማት እቅድ የተቀመጡ ግቦችን በማሳካት፣ አዳዳስ የስራ ሂደቶችን በስራ ላይ በማዋል እንዲሁም አገሪቱ የተቀበለቻቸውን አለም አቀፍ ስምምነቶችን በሚገባ ተፈጻሚ በማድረግ የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶችን መብትና ጥቅም በሚፈለገው መልኩ ከማስጠበቅ አኳያ አሁንም ትኩረት ሰጥቶ መስራት ከዘርፉ ይጠበቃል ሲሉ ሚኒስትሯ አክለዋል።
ለዚህምበትግበራ ሂደት ከነበሩ ክፍተቶችና ደካማ ጎኖች ትምህርት በመውሰድና ለሚያጋጥሙ ችግሮችም ዘላቂ መፍትሔ በማበጀት ለተሻለ አፈጻጸም መትጋት ያስፈልጋል ብለዋል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በቀጣይ የተገኙ ስኬታማ ተሞክሮዎችን ከማስፋፋትና ቅንጅታዊ አሰራሩን ከማጠናከር ጎኖ ለጎን የሴክተሩን የማስፈፀም አቅም ለማጎልበት የሚያግዙ ተግባራትን ለማከናወን እቅድ መያዙን ጠቁመዋል።
በአገር አቀፍ ደረጃ ለውጥ የሚያመጡ፣ ሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርጉና ስትራቴጂካዊ በሆኑ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ አዎንታዊ ሚና ለመወጣት የሚያስችሉ ሰፋፊ የንቅናቄ ስራዎች እንደሚካሄዱም ማመላከታቸውን ሚኒስቴሩ አስታውቋል።