ስርጭቱ እንደ አዲስ ያገረሸባት ደቡብ አፍሪካ ገደቦችን አስቀመጠች

         የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ

በደቡብ አፍሪካ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ከአንድ ሚሊየን መሻገራቸውን ተከትሎ የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ አዲስ ጠበቅ ያሉ ገደቦችን አውጥተዋል፡፡

ቤት ውስጥና ከቤት ውጪ ሰዎች መሰብሰብ፣ከመሸ በኋላ እንቅቃሴ ማድረግና ማንኛውም አይነት የአልኮል መጠጥም መሸጥ ተከልክሏል፡፡

ፕሬዝዳንት ራማፎሳ ደቡብ አፍሪካ በወረርሽኙ ምክንያት አስፈሪና አሳሳቢ ሁኔታ ላይ መድረሷን ጠቅሰው አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ ግድ አንዳላቸው አስረድተዋል፡፡

አንዳንድ ሆስፒታሎችና የሕክምና ማዕከላት በርካታ ሰዎችን ተቀብለው እያስተናዱ እንደሆነና የግብአት እጥረት እያጋጠማቸው ስለመሆኑም እየገለጹ ነው።

ይህንን ተከትሎ ፕሬዝዳንቱ ባስተላለፉት መልዕክት ”501.V2 የሚባል አዲስ የኮሮናቫይረስ ዝርያ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ተገኝቷል።

በአሁኑ ሰአት በርካታ ሰዎች በቫይረሱ እየተያዙ መሆኑ በጣም አሳሳቢ ያደርገዋል። የጥንቃቄ እርምጃዎቻችንን ችላ ማለታችን ነው ለዚህ ያበቃን” ብለዋል።

ፕሬዝዳንቱ አክለውም አዲሶቹ ጥብቅ ገደቦች ከሰኞ ምሽት ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚሆንና ቢያንስ ለሚቀጥሉት ሶስት ሳምንታት ተግባራዊ ሊሆን እንደሚችል አስረድተዋል።

”ከቀብር ስነ ስርአት ውጪ ማንኛውም አይነት ሰዎችን የሚያሰባስብ ማህበራዊ ክንውን ተከልክለሏል፣ ሰዎች ከመሸ በኋላ መንቀሳቀስ አይችሉም፣ ሁሉም ሱቆች፣ መጠጥ ቤቶችና ምግብ ቤቶች ልክ ከምሽቱ ሁለት አሰት ላይ መዘጋት አለባቸው” ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።

የአልኮል መጠጦችን መሸጥም ቢሆን የተከለከለ ሲሆን ህዝብ በሚበዛባቸው አካባቢዎች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማስክ ማድረግ ግዴታ  ነው ሲል ቢቢሲ አስነብቧል፡፡