ሶማሊያ ከኬንያ ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አቋረጠች


የሶማሊያ መንግሥት ከጎረቤት አገር ኬንያ ጋር ያለውን ዲፕሎማሲ ግንኙነት ማቋረጡን ዛሬ አስታወቀ።

ይህንንም ተከትሎ የሶማሊያ መንግሥት ናይሮቢ የሚገኙ ሁሉም ዲፕሎማቶቹ ኬንያ ለቀው እንዲወጡ ጥሪ ያደረገ ሲሆን፣ በተመሳሳይም በሞቃዲሹ የሚገኙ የኬንያ ዲፕሎማቶችም አገሪቱን ለቀው እንዲወጡ የሰባት ቀናት ቀነ ገደብ ሰጥቷል።

ይህ የተገለፀው የሶማሊያው የማስታወቂያ ሚኒስትር ኦስማን አቡካር ዱቤ ለመንግሥት ሚዲያ በሰጡት መግለጫ ነው።

ሚኒስትሩ “የሶማሊያ መንግሥት በዓለም አቀፍ ሕግና ሥርዓት በተረጋገጠው ብሔራዊ ሉዓላዊነቱ ላይ በመመስረት የአገሪቱን ሉዓላዊነት፣ አንድነት እና መረጋጋት የማስጠበቅ ሕገ መንግሥታዊ ግዴታውን በመወጣት ከኬንያ መንግሥት ጋር ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማቋረጥ ወስኗል” ብለዋል።

ውሳኔው የመጣው ሶማሊያ የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ለሆኑትና የወቅቱ የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ተቋም [ኢጋድ] ሊቀመንበር ለአብደላ ሃምዶክ በኬንያ ላይ የተቃውሞ ደብዳቤ ካስገባች በኋላ ነው።

በቅርቡ ኬንያ ሶማሊያን ለማበጣበጥና መረጋጋት እንዳይሰፍን እያሴረች ነው ሲሉ የሶማሊያ ማስታወቂያ ሚኒስትር ኦስማን አቡበከር ዱቤ ከሰው ነበር።

ሚኒስትሩ “ኬንያን እናከብራለን፤ በጉርብትና ላይ የተመሠረተ አብሮነትና መተጋገዝም እንዲኖር እንፈልጋለን። በእኛ በኩል እነዚህን እሴቶች አጠንክረን ይዘናል። ከኬንያ በኩል ግን በማይገባ የቀን ህልም የሶማሊያን መሬትና ውሃ መቆጣጠር ይፈልጋሉ” በማለት ነበር በብሔራዊ ቴሌቪዥኑ ፌስቡክ ገፅ በቀጥታ በተላለፈ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የተናገሩት።

ሚኒስትሩ እንደ ማስረጃ ያነሱትም ከኬንያ በኩል ፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነትና የሶማሊያ ተቃዋሚ መሪዎችን ናይሮቢ ማስተናገዷን ነው።

ከዚህ ቀደም ከደቡባዊ ሶማሊያ ጁባላንድ ግዛት የተወጣጡ ፖለቲከኞች በመጪው የሶማሊያ ምርጫ ላይ ውይይት አድርገዋል ተብሏል።

“ሞቃዲሾ አንድም ቢሆን የኬንያ ተቃዋሚ ፖለቲከኞችን አስተናግዳ አታውቅም። በጎረቤቶቻችን ላይ ውጥረት እንዲነግስም አንፈልግም ነገር ግን በሶማሊያ የሚሰነዘሩ ጥቃቶች መነሻቸው ከናይሮቢ ሆኗል። በሶማሊያ የሚደረሱ ስምምነቶች የሚጣሱበትም ቦታ ኬንያ ሆኗል” ነበር ያሉት ሚኒስትሩ በወቅቱ በሰጡት መግለጫቸው።

ከዚህም በተጨማሪ ኬንያ በአፍሪካ ሕብረት ሰላም አስከባሪ ኃይል (አሚሶም) ስር በሶማሊያ ያሰማራቻቸውን ወታደሮቿን ማስወጣቷን ተከትሎ ቁልፍ የሚባሉ ግዛቶቿ በአልሻባብ ቁጥጥር ሥር እንደወደቁ ሚኒስትሩ መጥቀሳቸው አይዘነጋም።

የኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በበኩሉ፣ በሶማሊያ የውስጥና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ጣልቃ ገብተዋል የሚለውን ጉዳይ ማጣጣላቸው ይታወሳል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።