ሶማሌላንድ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለሀገር መከላከያ ሠራዊት አምቡላንስ አበረከቱ

ሚያዚያ 20/2013 (ዋልታ) – በሶማሌላንድ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በትግራይ ክልል ህግ በማስከበር ዘመቻ ላይ ለተሰማራው የሀገር መከላከያ ሠራዊት 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ግምት ያለውና የተሟላ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ዘመናዊ አምቡላንስ አበርክተዋል።

በሶማሌላንድ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ቆንስል ጄኔራል አቶ ሰኢድ ሙሁመድ በሶማሌላንድ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ከዚህ ቀደምም በተለያዩ ሀገራዊ ጉዳዮች በንቃት መሳተፋቸውን ገልጸዋል፡፡

ለመከላከያ ሠራዊት 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው ይህን ዘመናዊ አምቡላንስ ድጋፍ በማድረጋቸው ለኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ምስጋና አቅርበዋል።

በርክክብ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የኢፌዲሪ መከላከያ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ  ወ/ሮ ማርታ ሊዊጂ ኮሚኒቲው ላደረገው ድጋፍ አመስግነዋል።

በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የኢፌዲሪ መከላከያ ሚኒስቴር ወታደራዊ አመራሮችና የሶማሌላንድ ኮሚኒቲ ተወካዮች መገኘታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡